ሶማሊላንድ የበርበራ ወደብና አውሮፕላን ማረፊያን አሜሪካ እንድትጠቀምበት ፈቀደች
ሶማሊ ላንድ በምትኩ ከአሜሪካ የሀገርነት እውቅና እንደምትፈልግ ገልጻለች
የሶማሊላንድ ፕሬዘዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ከአንድ ወር በኋላ ወደ ዋሸንገተን ያቀናሉ ተብሏል
ሶማሊላንድ የበርበራ ወደብን እና አውሮፕላ ማረፊያን አሜሪካ እንድትጠቀምበት መፍቀዷ ተሰምቷል።
የሶማሊያ አንድ አካል የሆነችው እና ራሷን እንደ አገር የምትቆጥረው ሶማሊላንድ የበርበራ ወደብን እና አውሮፕላን ጣቢያን አሜሪካ እንድትጠቀምበት መፍቀዷን ዎልሰትሪት ጆርናል ዘግቧል።
አሜሪካ በዚህ ወደብ እና የአውሮፕላን ጣቢያ ላይ ወታደራዊ አውሮፕላኖቿን እንድታሳርፍ መፍቀዷ ተገልጿል።
በምስራቅ አፍሪካ የቻይና እንቅስቃሴ እንዳሳሰባት የምትገልጸው አሜሪካ በበርበራ ወደብ አዲስ የጦር ሰፈር ልትገነባ እንደምትችልም ዘገባው አክሏል።
የራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዘዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ከአንድ ወር በኋላ ወደ ዋሸንገተን እንደሚያቀኑ የተገለጸ ሲሆን አዳዲስ ስምምነቶችን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ሶማሊላንድ ራሷን እንደ ሀገር የምትቆጥር ሲሆን አሜሪካን የሀገርነት እውቅና እንድትሰጣት በሚል የአውሮፕላን ማዘዣውን እና የበርበራ ወደብን እንድትጠቀምበት ፈቅዳለች።
የሶማሊያ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ በተደጋጋሚ መራዘም እንዳሳሰባት የምትገልጸው አሜሪካ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የደረሰችበት ስምምነት ሶማሊያን ሊያስቆጣ እንደሚችል ይጠበቃል።
አሜሪካ የበርበራ ወደብን እና አውሮፕላን ማረፊያን እንድትጠቀም የተፈቀደላት ከሶማሊያ መንግስት እውቅና ውጪ መሆኑ እና አለመሆኑ እስካሁን ከሁለቱም ወገን የተገጸ ነገር የለም።
አሜሪካ በአፍሪካ ትልቁን የጦር ሰፈር በጅቡቲ የመሰረተች ሲሆን፤ ቻይናም በጥቂት ርቀት ውስጥ በጅቡቲ ባብ ኤል ማንዴብ ላይ በ2017 መመስረቷ ይታወሳል።
ቻይና በምዕራብ አፍሪካ ተመሳሳይ የጦር ሰፈር በኢኳቶሪያል ጊኒ ለመገንባት በሂደት ላይ ስትሆን፤ አሜሪካ የቻይና እቅድ እንዳይሳካ የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ እንደሆነች በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ሶማሊላንድ ከፈረንጆቹ 1991 ዓመት ጀምሮ ከሶማሊያ መገንጠሏን እና የራሷን መገበያያ ገንዘብ፣ ሰንደቅ አላማ እና ሌሎች አንደ አገር ሊያስቆጥራት የሚችሉ እርምጃዎችን የወሰደች ቢሆንም፤ እስካሁን ድረስ የትኛውም ሀገር የሀገርነት እውቅና የሰጣት የለም።
የበርበራ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ከወራት በፊት የተጠናቀቀ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአውሮፕላን ማረፊያ አውሮፕኑን ያሳረፈ የመጀመሪያው አየር መንገድ ነበር።