የአረብና ሙስሊም ሀገራት የሚኒስትሮች ልኡክ ቻይና ገብቷል
ልኡኩ በጋዛ ተኩስ እንዲቆም በጸጥታው ምክርቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላት ቤጂንግ ጫና እንድትፈጥር ያግባባል ተብሏል
ቻይና በጋዛ ተኩስ እንዲቆም ከመጠየቅ ውጭ ሃማስን አለማውገዟ እስራኤልን ማስቆጣቱ ይታወሳል
የአረብና ሙስሊም ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ልኡክ ቻይና ገብቷል።
የሳኡዲ አረቢያ፣ ግብጽ፣ ዮርዳኖስ፣ ኢንዶኔዥያና ፍልስጤም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የእስላሚክ ትብብር ድርጅትና ሌሎች ተቋማት መሪዎችን ያካተተው ልኡክ ከቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ ጋር መክሯል።
“እዚህ (ቤጂንግ) የተገኘነው ግልጽ መልዕክት ለማስተላለፍ ነው፤ በጋዛ ጦርነት እና እልቂቱ መቆም አለበት፤ የሰብአዊ ድጋፍም በፍጥነት መድረስ አለበት” ብለዋል የሳኡዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልኡል ፋይሰል ቢን ፋርሃን አል ሳኡድ።
የቻይናው አቻቸው ዋንግ ይ በበኩላቸው የፍልስጤማውያን ነጻ ሀገር የመመስረት ፍትሃዊ ጥያቄ ሊመለስ እንደሚገባውና ቤጂንግ የአረብና ሙስሊም ሀገራት ወዳጅ ሆና እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
ሚኒስትሩ የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ እስራኤል ተኩስ እንድታቆም ከመጠየቅ ውጭ አንድም ጊዜ ሃማስን አለማውገዛቸው ቴል አቪቭን አስቆጥቶ እንደነበር ይታወሳል።
የአረብና ሙስሊም ሀገራት የሚኒስትሮች ልኡኩ በጋዛ ተኩስ ስለሚቆምበት እና በሃማስ የታገቱ ሰዎች ስለሚለቀቁበት ሁኔታ ከቻይና ባለስልጣናት ጋር ምክክር አድርጓል።
ሳኡዲ በያዝነው ህዳር ወር በጠራቻቸው አስቸኳይ ጉባኤዎች በጋዛ አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ መጠየቋ እና የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት በጋዛ የተፈጸሙ “የጦር ወንጀሎችን” እንዲያጣራ መጠየቋ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ከ13 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈው ጦርነት እስካሁን መቆም አልቻለም።
የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤትም በአሜሪካ ድምጽን በድምጽ የመሻር ስልጣን ምክንያት በጋዛ ተኩስ እንዲቆም የቀረቡ የውሳኔ ሃሳቦችን ውድቅ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
የአረብና ሙስሊም ሀገራት የሚኒስትሮች ልኡኩ በቀጣይም በጸጥታው ምክርቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር ስልጣን ወዳላቸው ሀገራት(አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ) ጉዞ ያደርጋል ተብሏል።