የአረብ ሀገራት መሪዎች በጋዛ መልሶ ግንባታ እቅድ ዙሪያ ዛሬ በሪያድ ይመክራሉ
በውይይቱ ትራምፕ ፍልስጤማውያንን እንዲያስጠልሉ የጠየቋቸው የግብጽና ዮርዳኖስን ጨምሮ የባህረ ሰላጤው ሀገራት መሪዎች ይሳተፋሉ

የመንግስታቱ ድርጅት የፈራረሰችውን ጋዛ መልሶ ለመገንባት በጥቂቱ 53 ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋል ብሏል
የአረብ ሀገራት መሪዎች ግብጽ ባቀረበችው የጋዛ መልሶ ግንባታ እቅድ ዙሪያ ዛሬ በሪያድ ይመክራሉ።
የሳኡዲ ልኡል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ከግብጽ፣ ዮርዳኖስ፣ አረብ ኤምሬትስ፣ ኩዌት፣ ኳታር፣ ኦማ እና ባህሬን መሪዎች ጋር "መደበኛ ያልሆነ ወንድማዊ" ምክክር ያደርጋሉ ብሏል የሳኡዲ ዜና አገልግሎት።
የፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ በውይይቱ እንዲሳተፉ መጋበዛቸውን ዘ ናሽናል ከምንጮቹ ማረጋገጡን በመጥቀስ ዘግቧል።
መሪዎቹ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፍልስጤማውያንን አፈናቅለው ጋዛን ለመቆጣጠር የያዙትን እቅድ ሲያወግዙ ቆይተዋል።
በዛሬው ምክክራቸውም ካይሮ የትራምፕን የጋዛ እቅድ የሚተካና ፍልስጤማውያንን ከርስታቸው የማያፈናቅል ነው በሚል ባቀረበችው የጋዛ መልሶ ማልማት እቅድ ዙሪያ ይወያያሉ ነው የተባለው።
በሪያዱ ምክክር መሪዎቹ የሚደርሱት ስምምነት ከ11 ቀናት በኋላ በካይሮ በሚካሄደው የአረብ ሊግ አስቸኳይ ጉባኤ ላይ ለውይይት እንደሚቀርብ የሳኡዲ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።
የመንግስታቱ ድርጅት፣ የአለም ባንክ እና የአውሮፓ ህብረት ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ባደረጉት የጋራ ሪፖርት ጋዛን መልሶ ለመገንባት በጥቂቱ 53.2 ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋል ብለዋል።
እስራኤል ለ15 ወራት በጋዛ የፈጸመችው ድብደባ የፍልስጤምን መሰረተ ልማቶች ማውደሙን ያነሳው ሪፖርቱ፥ የሰርጡን ኢኮኖሚ ክፉኛ ማንኮታኮቱንም አብራርቷል።
ከጋዛ ቤቶች ውስጥ 53 በመቶው መውደማቸውን በመጥቀስም የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት 30 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ ነው የጠቆመው።
ጦርነቱ በጋዛ ያደረሰውን የኢኮኖሚ ጉዳት ለመጠገንም በጥቂቱ 19 ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋል ብሏል።
የመንግስታቱ ድርጅት በቅርቡ ይፋ ባደረገው የጉዳት ግምገማ ሪፖርት በእስራኤል የቦምብ ጥቃት የተከመረውን ከ50 ሚሊዮን ቶን በላይ የሚመዝን ፍርስራሽ ለማጽዳት 21 አመታትን ሊወስድ እንደሚችል መጠቆሙ ይታወሳል፡፡
የጋዛን የፈራረሱ ህንጻዎች እና ቤቶች ዳግም ለመገንባትም እስከ 15 አመታት ይወስዳል ማለቱ አይዘነጋም።