አረብ ኤምሬትስ ፍልስጤማውያንን ከጋዛ የማፈናቀል እቅድ እንድምትቃወም አስታወቀች
ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋር በአቡ ዳቢ ተወያይተዋል

የአረብ ሀገራት መሪዎች በትራምፕ የጋዛ እቅድ ዙሪያ በያዝነው የካቲት ወር በሪያድ እንደሚመክሩ ይጠበቃል
አረብ ኤምሬትስ ፍልስጤማውያንን ከጋዛ የማፈናቀል እቅድ እንድምትቃወም አስታወቀች።
በእስራኤል የመጀመሪያ የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝታቸውን ያደረጉት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ዛሬ ኤምሬትስ ገብተዋል።
የኤምሬትስ ፕሬዝዳንት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን በአቡ ዳቢ ተቀብለው ሲያነጋግሩ ሀገራቸው ፍልስጤማውያንን ከመሬታቸው የማስወጣት እቅድ እንደማትቀበል ነግረዋቸዋል ብሏል የኤምሬትስ የዜና ወኪል ዋም።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይፋ ያደረጉትን ጋዛን የመጠቅለል እና ፍልስጤማውያንን በግብጽ እና ዮርዳኖስ የማስፈር እቅድ በአረብ ሀገራት ከፍተኛ ውግዘት ገጥሞታል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስርት በሳኡዲ ጉብኝት ሲያደርጉ ሪያድ እቅዱን እንደምትቃወመው ያስታወቀች ሲሆን፥ አቡ ዳቢም ተመሳሳይ አቋሟን ገልጻለች።
የእስራኤል እና ፍልስጤም ግጭት የሚፈታው "በሁለት ሀገር መፍትሄ" መሆኑንና የፈራረሰችውን ጋዛ ዳግም የመገንባቱ ሂደት ነዋሪዎችን በማፈናቀል ሊሆን እንደማይገባው ማንሳታቸውንም ዋም ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ የግጭቱን መስፋፋት ማስቆም ካልተቻለ ለመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ከፍተኛ የደህንነት ስጋት እንደሚደቅንም አሳስበዋል።
የኤምሬትስ ፕሬዝዳንት እና የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከጋዛ ወቅታዊ ሁኔታ ባሻገር የአሜሪካ እና ኤምሬትስን ትብብር በሚያሳድጉ ዘርፎች ላይ ተወያይተዋል።
የአረብ ሀገራት መሪዎች አሁንም ድረስ አነጋጋሪነቱ በቀጠለው የትራምፕ የጋዛ እቅድ ዙሪያ በያዝነው የካቲት ወር በሪያድ እንደሚመክሩ ሬውተርስ ዘግቧል።
በሪያዱ ምክክር የአረብ ኤምሬትስ፣ ግብጽ፣ ዮርዳኖስ፣ ሳኡዲ እና ኳታር መሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን፥ የአረብ ሊግም በመጋቢት ወር በሚያካሂደው ጉባኤ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚመክር ተገልጿል።