“የትኛውም ኃይል ፍልስጤማውያንን ከትውልድ ሀገራቸው ማስወጣት አይችልም”- ኤርዶጋን
ኤርዶጋን “ጋዛ፣ ዌስት ባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌም የፍልስጤማውያን ናቸው” ብለዋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/10/252-104014-whatsapp-image-2025-02-10-at-9.39.25-am_700x400.jpeg)
ትራምፕ ጋዛን ለመቆጣጠር የያዙትን እቅድ በርካታ የዓለም ሀገራት በመቃወም ላይ ይገኛሉ
ቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን “የትኛውም ኃይል ፍልስጤማውያንን ከትውልድ ሀገራቸው ማስወጣት አይችልም” አሉ።
ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ትራምፕ ጋዛን ለመቆጣጠር የያዙትን እቅድ ውድቅ በማድረግ መግለጫ ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን በመግለጫቸውም “የትኛውም አይነት ኃይል የጋዛ ነዋሪዎችን ከዘላለማዊ የትውልድ ሀገራቸው ማስወጣት አይችልም” ሲሉ አረጋግጠዋል።
“ጋዛ፣ ዌስት ባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌም የፍልስጤማውያን ናቸው” ሲሉም ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ትናንት ምሽት በኢስታቡል በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ትራምፕ ፍሊስጠየማውያንን ወደ ሌላ ቦታ በማዘዋወር ጋዛን ለመቆጣጠር የያዙትን እቅድ ያነሱ ሲሆን፤ የአሜሪካ አስተዳር በጺዮናዊ አስተዳር ተገፋፍቶ ያወጣው እቅድ መሆኑን እና ለውይይት የማይበቃ እርባና ቢስ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይትሃውስ እንደገቡ የጋዛ ፍርስራሽ እስኪጸዳ ድረስ ፍልስጤማውያን እንደ ግብጽ እና ዮርዳኖስ ባሉ ሀገራት እንዲጠለሉ ሃሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ዶናልድ ትራምፕ ጋዛን ለመቆጣጠር የያዙትን እቅድ በርካታ የዓለም ሀገራት በመቃወም ላይ ይገኛሉ።
የጋዛ ተፈናቃዮችን በቋሚነት እና በጊዜያዊነት እንዲያስጠልሉ ከትራምፕ ትእዛዝ የተሰጣቸው ግብጽ እና ዮርዳኖስ እቅዱን ውድቅ ያደረጉት ሲሆን፥ የፍልስጤም እና የአረብ መሪዎችም አጥብቀው ተቃውመውታል።
በትራምፕ ውሳኔ የተገረሙ እና የተደናገጡ የጋዛ ነዋሪ ፍሊጤየማውያንም “ጋዛን ለቀን አንወጣም” ሲሉ ተቃውሞዋቸውን አሰምተዋል።
“ነፍሳችንን ቢያስከፍለን እንኳን ጋዛን አንለቅም” ያሉት የጋዛ ነዋሪ ፍሊስጤማውያን፤ “የትራምፕን ውሳኔ እንቃወማለን፣ ጦርቱን አስቁሟል፤ ነገር ግን እኛን ማፈናቀል ህይወታችን እንዲያበቃለት ያደርጋል” ብለዋል።
በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምት መደረሱን ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍሊስጤማውያን ወደ ፈራረሰቸው መንደራቸው እየተመሙ ይገኛሉ።
እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት ከሆነ ከአጠቃላይ የጋዛ ነዋሪዎች መካከል 1.9 ሚሊየን ወይም 90 በመቶው በ15 ወሩ ጦርት ከመኖሪያቸው ለመፈናቀል ተገደዋል።