ግብጽ ፍልስጤማውያን ሳይፈናቀሉ ጋዛን ለመገንባት የሚያስችል እቅድ እንደምታቀርብ ገለጸች
ፕሬዝደንት ትራምፕ ጋዛን የመቆጣጠርና ፍልስጤማውያንን ወደ ግብጽና ጆርዳን የማዛወር እቅዳቸው ተግባራዊ እንዲሆን ጫና እያደረጉ ይገኛሉ
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/12/243-131055-img-20250212-121029-774_700x400.jpg)
15 ወራት የዘለቀውን ጦርነት ያስቆመው የእስራኤል-ሀማስ ተኩስ አቁም ስምምነትም አሁን ላይ አደጋው ውስጥ ገብቷል
ግብጽ ፍልስጤማውያን ከቦታቸው ሳይፈናቀሉ ጋዛን መልሶ ለመገንባት የሚያስችል "የተሟላ እቅድ" ለማዘጋጀት ማቀዷን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ግብጽ በቀጠናው የተሟላና ፍትሃዊ የሆነ ሰላም እንዲሰፍን ከአሜሪካው ፕሬዝደንት ትራምፕ ጋር ለመተባበር ዝግጁ ናት ብሏል።
መግለጫው የወጣው ፕሬዝደንት ትራምፕ ጋዛን የመቆጣጠርና ፍልስጤማውያንን ወደ ግብጽና ጆርዳን የማዛወር እቅዳቸው ተግባራዊ እንዲሆን ጫና እያደረጉ ባለበት ወቅት ነው።
ፕሬዝደንት ትራምፕ በትናንትናው እለት በኃይትሀወስ ያገኟቸው የጆርዳኑ ንጉስ አብዱላህ ይህንኑ እቅዳቸውን እንዲቀበሏቸው ጫና አድርገውባቸዋል።
"እንቆጣጠራታለን፤እንኒዘዋለን። አልምተን ለመካከለኛው ምስራቅ ብዙ የስራ እድል እንፈጥራለን" ሲሉ የተናገሩት ትራምፕ እቅዳቸው በቀጣናው ሰላም ያመጣል ብለዋል።
ነገርግን ንጉሱ የትራምፕን እቅድ አልተቀበሉትም።
ንጉስ አብዱላህ ቆይት ብለው እንደናገሩት የጆርዳን አጎራባች በሆነው ዌስትባንክ ጨምሮ ፍልስጤማውያንን ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር እንደማይቀበሉ ተናግረዋል። "ይህ የአረብ ሀገራት አቋም ነው" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
"ፍልስጤማውያንን ሳናፈናቅል አስከፊ የሆነውን የሰብአዊ ቀውስ እንዴት እንፍታው ለሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው ነው።"
የጆርዳኑ አቻቸው ይህን ቢሉም ትራምፕ ግን ግብጽና ጆርዳን በመጨረሻ ፍልስጤማውያንን ለማስጠለል መስማማታቸው አይቀርም ብለዋል።
ሁለቱ ሀገራት ከአሜሪካ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድጋፍ የሚያገኙ ናቸው።
የአረብ ሀገራትና የፍልስጤም ባለስልጣናት የፍልስጤማውያንን ከጋዛ ማፈናቀል ተግባር በጽኑ እንደሚቃወሙት ቀደም ሲል ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጻፉት ደብዳቤ ግልጽ አድርጠዋል።
15 ወራት የዘለቀውን ጦርነት ያስቆመው የእስራኤል-ሀማስ ተኩስ አቁም ስምምነትም አሁን ላይ አደጋው ውስጥ ገብቷል። ትራምፕና ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ሀማስ በእጁ ያሉ ሁሉንም ታጋቾች በመጭው ቅዳሜ የማይለቅ ከሆነ ስምምነቱ እንደሚፈርስ ዝተዋል።