ሄዝቦላህ መሪው ከተገደለበት በኋላ በመጀመሪያ እርምጃው በርካታ ሮኬቶችን ወደ ኤስራኤል ተኩሷል
በእስራኤል እና በሊባኖስ የሚንቀሳቀሰው የሄዝቦላህ ቡድን መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት እያገረገሸ እና መጠነ ሰፊ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል።
በሊባኖስ የመገናኛ መሳርያዎች ላይ የተገጠሙ ፈንጂዎችን በማፈንዳት ጥቃት ማድረስ የጀመረችው እስራኤል ከሰኞ ጀምሮ መጠኑ ከፍ ያለ የአየር እና የሚሳኤል ጥቃት በሊባኖስ ላይ እየፈጸመች ትገኛለች።
ሄዝቦላህ ለእስራኤል እየሰጠ በሚገኝው ምላሽ እስከዛሬ በቡድኑ ጥቅም ላይ ውለው የማያውቁ ባላስቲክ ሚሳኤሎችን ጭምር በመጠቀም በማዕከላዊ እስራኤል ጥቃት እየፈጸመ ይገኛል።
ምን አዳዲስ ክስተቶች ተስተናግደዋል?
እስራኤል በሊባኖስ ውስጥ የሚገኙ የሄዝቦላህ ኢላማዎች ላይ የምትፈጽመውን ጥቃቶች የቀጠለች ሲሆን፤ የሮኬት ማስወንጨፊያዎች እና የመሳሪያ ማከማቻ ህንጻዎች ኢላማ መደረጋቸውን የእስራኤል ጦር አስታውቋል።
እስራኤል ዛሬ እሁድ በሊባስ የተለያዩ አካባቢዎች እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ 21 ሰዎች ሲሞቱ፤ 47 መቁሰላቸውን የሊባስ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ትናንት አዳሩን እስራኤል በሊባኖስ በፈጸመችው ጥቃት 33 ሰዎች ሲሞቱ፤ 195 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ሄዝቦላህ መሪው ከተገደለበት በኋላ በእስራኤል ላይ የመጀመሪያ እርምጃ የወሰደ ሲሆን፤ በዚህም አዳሩን በርካታ ሮኬቶችን ወደ ኤስራኤል ተኩሷል።
እስራኤል ባሳለፍነው አርብ ሌሊት በቤሩት በፈጸመችው ጥቃት የሊብኖሱ ሄዝቦላህ መሪ ሼክ ሀሰን ናስራላህን መግደሏ ተሰምቷል።
ሄዝቦላህ መሪው ሀሰን ናስራላህ እስራኤል በቤሩት በፈጸመችው ጥቃት መገደላቸውን ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ አረጋገጧል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያመኒን ኔታንያሁ፤ “እስራኤል ሀሰን ነስረላህን በመግደል ነጥብ አስቆጥራለች፤ የነስረላህ መገደል ታሪካዊ እና ጨዋታ ቀያሪ ነጥብ ነው” ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የነስረላህን መገደል ለ40 ዓመተት የነገሰው የሽብር ዘውድ ላይ “ለህፍትህ የተወሰደ እርምጃ” ሲሉ ያወደሱ ሲሆን፤ በሄዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል የተኩስ አቁም አንዲደረግም በድጋ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ ሀምኒ፤ የነስረላህ ግድያ ያለበቀል እርምጃ አይታለፍም ያሉ ሲሆን፤ በመላው ኢራንም የአምስት ቀናት ብሄራዊ የሀዘን ቀን አውጀዋል።
የሄዝቦላህ ቁልፍ አጋር የሆነችው ኢራን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አበሊባስ ጉዳይ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርባለች።
የእስራኤል- ሄዝቦላህ ግጭት ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ
የእስራኤል ጥቃት በመላው ሊባኖስ ከፍተኛ ስጋትን እና ውጥረትን የፈጠረ ሲሆን፤ በደቡብ እና ምስራቅ ሊባኖስ ውስጥ የሚኖሩ በርካቶችም መኖሪያቸውን ለቀው እየወጡ ይገኛሉ።
የተባሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኃላፊ ፊሊፖ ግራንዲ፤ በሊባኖስ ውስጥ ብቻ ከ200 ሺህ በላይ ሊባኖሳውያን መፈናቀላቸውን አስታውቀው፤ ከ50 ሺህ በላይ ሊባኖሳውያን ደግሞ ወደ ጎረቤት ሀገር ሶሪያ መሰደዳቸውን አስታውቀዋል።
ከ70 ሺህ በላይ እስራኤላውያንም በሄዝቦላህ እና እስራኤል ድንበር ላይ የተኩስ ለውውጥ ከተጀመረ ወዲህ ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን አስታውቀዋል።