የሄዝቦላ ዋና ጸኃፊ ሀሰን ነስረላህ የተገደለው የእስራኤል ጦር በትናንትናው እለት በቤሩት በፈጸመው የአየር ድብደባ ነው ተብሏል
እስራኤል የሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ነስረላህን ገደልኩ አለች።
የእስራኤል ጦር በትናንትናው እለት በቤሩት በፈጸመው የአየር ጥቃት የሄዝቦላን ዋና ጸኃፊ ሀሰን ነስረላህን መግደሉን ማስታወቁን ሲኤንኤን እና ታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘግበዋል።
ሄዝቦላ በዚህ ጉዳይ እስካሁን መልስ አለመስጠቱ ተገልጿል።
እስራኤል በትናንትናው እለት በቤሩት ዳርቻ በሚገኘው የሄዝቦላ ዋና ማዘዣ ጣቢያ ላይ ጥቃት የሰነዘረችው የቡድኑን ዋና አዛዥ ለመግደል ነበር ተብሏል።
እስራኤል ከባለፈው ሰኞ እለት ጀምሮ ሊባኖስ ውስጥ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ከ800 በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በመቶሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ከቤታቸው ተፈናቅለዋል።
እስራኤል እየፈጸመችው ባለው ጥቃት የሄዝቦላ መሪዎች ዋነኛ ኢላማዎች ናቸው።
በፍልስጤሙ ሀማስ ላይ ለወራት ዘመቻ ካካሄደች በኋላ አሁን ትኩረቷን ወደ ሊባኖሱ ሄዝቦላ ያዞረችው እስራኤል፣ በቀጣናው ላለው ግጭት ኢራንን ዋና ተጠያቂ አድርጋለች።
እየተዋጋን ያለነው ሊያጠፉን ከሚሹ “አረመኔ ጠላቶች ጋር ነው" ያሉት ኔታንያሁ “እስራኤል ኢራን በከፈተችው 7 አውደ ውግያዎች እየተዋጋች ትገኛለች፤ ተሄራን ከምታሰማራቸው ርህራሄ የለሽ ገዳዮች እራሳችንን መከላከላችንን እንቀጥላለን"ብለዋል።
ኔታንያሁ "በኢራን ውስጥ የእስራኤል ረጅም ክንድ የማይደርስበት ቦታ አለመኖሩ ሊታሰብበት ይገባል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
እስራኤል ቀይ መስመሬን እያለፈች ነው ያለችው ኢራን፣ እስራኤል ከአሜሪካ ያገኘችውን 'በንከር በስተር' የተባለ ቦምብ በመጠቀም ቤሩትን ደብድባለች የሚል ክስ አቅርባለች።
በሊባኖስ የጀመረችውን ጥቃት እንድታቆም ጫና ቢደረግባትም፣ ከጋዛ ወደ ሊባኖስ ትኩረቷን ያደረገችው እስራኤል ተፈናቃዮችን መመለስን ጨምሮ ሁሉም ግቦቿ እስከሚሳኩ ድረስ ማጥቃቷን እንደምትገፋበት ገልጻለች።