የአረብ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትራምፕ ፍልስጤማውያንን በተመለከተ ስላቀረቡት ጥሪ ምን አሉ?
ፍልስጤማውያንን ከጋዛ የማስወጣት ሀሳብ የጋዛ ጦርነት ከተጀመረበት ከጥቅምት 2023 ጀምሮ በአጎራባች የአረብ ሀገራት በተደጋጋሚ ውድቅ ተደርጓል
ትራምፕ ባለፈው ሳምንት የፈራረሰችው ጋዛ እስከምትጸዳ ድረስ ግብጽና ጆርዳን ፍልስጤማውያንን ማስጠለል አለባቸው የሚል አወዛጋቢ አስተያየት ሰጥተዋል
የአረብ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የአሜሪካው ፕሬዝደንት ትራምፕ በጋዛ ሰርጥ ያሉ ፍልስጤማውያንን ወደ ግብጽና ጆርዳን እንዲዛወሩ ያቀረቡትን ጥሪ በትናንትናው እለት ውድቅ በማድረግ አንድ አይነት አቋም አንጸባርቀዋል።
ከግብጽ፣ ጆርዳን፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ኳታር፣ አረብ ኢምሬትስ፣ የፍልስጤም አስተዳደርና ከአረብ ሊግ የመጡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ባለስልጣናት በካይሮ ስብሰባ ካደረጉ በኋላ ባወጡት የጋራ መግለጫ እንዲህ አይነት እርምጃ የቀጣናውን አለመረጋጋት አደጋ ውስጥ የሚጥል፣ ግጭት የሚያስፋፋና ሰላም እንዳይመጣ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
"በማስፈር እንቅስቃሴ ወይም በማፈናቀል ወይም አፈናቅሎ ቦታቸውን በመውሰዱ የሚደረገውን የፍልስጤማውያንን የማይገረሰስ መብት የመንፈግ ጥረትን ውድቅ ማድረጋችንን እናረጋግጣለን " ብሏል የጋራ መግለጫው።
ሀገራቱ አክለውም የእስራኤልና ፍልስጤምን ሁለት ሀገርነት ወይም "ቱ ስቴት ሶሉሽንስ" መሰረት በማድረግ በመካከለኛው ምስራቅ ፍትህና ሰላም እንዲሰፍን ከትራምፕ አስተዳደር ጋር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ስብሰባ የተደረገው ባለፈው ሳምንት ትራምፕ ለ15 ወራት በዘለቀው ጦርነት የፈራረሰችው ጋዛ እስከምትጸዳ ድረስ ግብጽና ጆርዳን ፍልስጤማውያንን ማስጠለል አለባቸው የሚል አወዛጋቢ አስተያየት መስጠታቸውን ተከትሎ ነው።
ተችዎት የትራምፕ ንግግር ከዘር ማጽዳት ጋር የሚስተካከል ነው ሲሉ ገልጸውታል።
የግብጹ ፕሬዝደንት አብዱልፋታህ አል ሲሲ ግብጽ የፍልስጤማውያንን መፈናቀል ማመቻቸት አለባት የሚለውን ሀሳብ ባለፈው ረቡዕ እለት ውድቅ አድርገውታል።
ነገርግን ትራምፕ ለጆርዳንና ግብጹ ያደረጉትን ወታደራዊ ድጋፍ ጭምር በመጥቀስ"ብዙ እረድተናቸዋል፤ ያደርጉታል"ሲሉ በድጋሚ ሀሙስ እለት ሀሳባቸውን አጠናክረዋል።
ፍልስጤማውያንን ከጋዛ የማስወጣት ሀሳብ የጋዛ ጦርነት ከተጀመረበት ከጥቅምት 2023 ጀምሮ በአጎራባች የአረብ ሀገራት በተደጋጋሚ ውድቅ ተደርጓል።
በርካታ ሚሊዮን ፍልስጤማውያን በጆርዳን የሚኖሩ ሲሆን በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በግብጹ ተጠልለዋል። ሚኒስተሮቹ ግብጹ በ15 ወራት ጦርነት የወደመችውን ጋዛ መልሶ ለመገንባት ከተመድ ጋር በመተባበር አለምአቀፍ ስብሰባ ለማድረግ ያሰበችውን አለምአቀፍ ደግፈውታል። ስብሰባው የሚካሄድበት ቀን ይፋ አልሆነም።