የአለም ጤና ድርጅት ወረረርሽኙን ለመቆጣጠር 1 ሚሊየን ዶላር መድቧል
በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ ዳግም መቀስቀሱ ተነገረ፡፡
የኡጋንዳ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በዋና ከተማዋ ካምፓላ አዲስ የኢቦላ ቫይረስ መከሰቱን አረጋግጦ አንድ የ32 ዓመት ወንድ ነርስ በበሽታው ህይወቱ ማለፉን ገልጿል፡፡
ሟቹ የጤና ባለሙያ ከፍተኛ ትኩሳት፣ የደረት ሕመም፣ የመተንፈስ ችግር እና ከበርካታ የሰውነት ክፍሎቹ ደም ይፈሰው እንደነበር አስታውቋል፡፡
ከመሞቱ እና በሽታው ኢቦላ መሆኑ ከመታወቁ በፊት ሟቹ ነርስ በኬንያ አዋሳኝ በሆነችው ምባሌ በሚገኝው የህዝብ ሆስፒታልን ጨምሮ ወደ በርካታ የጤና ተቋማት እና የባህል ህክምና ባለሙያዎች ጋር ለህክምና ሄዶ እንደነበር ታውቋል።
የኡጋንዳ የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ሟቹ ከ44 ሰዎች እና ከ30 የጤና አጠባበቅ ሰራተኞች ጋር ንክኪ በመፍጠሩ እነዚህን ሰዎች ለመለየት እና ወደ ማቆያ ለማስገባት ግብረ ሀይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው፡፡
ነገር ግን ከአራት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በሚኖርባት እና ወደ ደቡብ ሱዳን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሩዋንዳ እና ሌሎች አጎራባች አገሮች የጉዞ ዋና ማዕከል ሆና በምታገለግለው ካምፓላ ከበሽታው ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ፈልጎ ለመለየት አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል፡፡
ኢቦላ 6 የታወቁ የቫይረስ ዝርያዎች ሲኖሩት ከእነዚህ ውስጥ አራቱ ማለትም ዛየር፣ ቡንዲቡግዮ፣ ሱዳን እና ታኢ ፎረስት የተባሉት በሰዎች ላይ ሞትን የማስከተል እድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ሱዳን የተባለው የኢቦላ ቫይረስ አይነት በከፍተኛ ደረጃ ተላላፊ ፣ የደም መፍሰስ ፣ ትኩሳት እና ሌሎችም የህመም ምልክቶችን በፍጥነት የሚያሳይ ሲሆን አሁን በዩጋንዳ የተከሰተውም ይሄው የቫይረስ አይነት መሆኑ ተሰምቷል፡፡
የኢቦላ ቫይረስ ምልክቶች ትኩሳት ፣ ድካም ፣ የጡንቻ ህመም ፣ ራስ ምታት እና የጉሮሮ ህመም ፣ ማስታወክ ፣ ተቅማጥ ፣ ሽፍታ እና የውስጥ እና የውጭ ደም መፍሰስ ናቸው።
የዓለም ጤና ድርጅት ኢቦላ በአማካይ ከ10 ሰዎች መካከል አምስቱን እንደሚገድል ይገልጻል።
ነገር ግን፣ ያለፉት ወረርሽኞች እንደየሁኔታው እና የምላሽ እርምጃዎች ከ25 በመቶ እስከ 90 በመቶ የሚደርስ የሞት መጠን አሳይተዋል።
ዩጋንዳ ከፈረንጆቹ 2000 ወዲህ የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ ሲከሰትባት ይህ ለዘጠነኛ ጊዜ ነው፡፡