የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሀፊ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ መከልከላቸውን አስታወቁ
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በአሜሪካ የነበራቸውን አገልግሎት ጨርሰው ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ እንዳይገቡ ተከልክለው ወደመጡበት መመለሳቸውን ተናግረዋል
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሀፊው ባለፈው አመት ከተፈጠረው ህገወጥ የኢጺስ ቆጾሳት ሹመት ጋር በተያያዘ መግለጫዎችን በመስጠት ይታወቃሉ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሃፊ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡ መከልከላቸውን ገለጹ።
የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፥ በአሜሪካ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ዛሬ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ነው ለቤተክርስቲያኗ ቴሌቪዥን ጣቢያ የተናገሩት።
“ደህንነቶች ፓስፖርትህን አንፈልግም ግሪን ካርድህን ነው ምንፈልገው ብለው ወደ መጣሁበት አሜሪካ መለሱኝ” ያሉት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፥ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ የተከለከሉበትን ምክንያት አልገለጹም።
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሃፊው ከዱባይ ወደ አሜሪካ በግዳጅ እንዲመለሱ መደረጉን የጠቀሰው የቴሌቪዥን ጣቢያው ፥ በጉዳዩ ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘግቧል።
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ከሳምንታት በፊት በቋሚ ሲኖዶስና በፓትርያርኩ እውቅና ወደ ሀገረ ስብከታቸው አሜሪካ ማምራታቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ምክንያት የሆነው ጉዳይ አልታወቀም።
ቤተክርስቲያኗ ባለፈው አመት ከተፈጠረው ህገወጥ የኢጺስ ቆጾሳት ሹመት ጋር በተያያዘ ከመንግስት ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብታ እንደነበር የሚታወስ ነው።
በወቅቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ባወጣው መግለጫ መንግስት ህጋዊ ሰውነት ያላትን ቤተክርስቲያኗን እና ከቀኖና ያፈነገጡ አባቶችን አኩል ማየቱ አግባብ አይደለም የሚል ወቀሳ ማቅረቧም አይዘነጋም።
ከዚህ አልፎም መንግስት አጥቢያ ቤተክርስቲያናት ጥቃት ሲደርስባቸው እና ንብረቷ ሲወድም ህግ አላስከበረም የሚል ክስ አቅርባም ነበር።
በወቅቱ የነበረውን አለመግባባት በተመለከተ በቴሌቪዥን ጣቢያዎች በመገኘት መግለጫ በመስጠትና የቤተክርስቲያኗን አቋም በማንጸባረቁ ረገድ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሃፊው ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ትልቅ ድርሻ እንደነበራቸው ይታወሳል።