ቤተክርስቲያኗ በትግራይ ክልል በተደረገው ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት "በእጅጉ አዝኛለሁ" አለች
"የትግራይ መንበረ ሰላም ከሳቴ ብርሃን" ለስድስት ኤጲስ ቆጶሳት ሲመት ሰጥቷል
ውሳኔ ለመስጠት አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ለሀምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. መጠራቱን ሲኖዶሱ አስታውቋል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በትግራይ ክልል ሀምሌ 15 እና 16፤ 2015 ዓ.ም.የተከናወነውን ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት "ህገ ወጥ" ነው ብላዋለች።
- ቤተክርስቲያኗ ጠ/ሚንስትር አብይና አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ ይካሄዳል የተባለውን የኤጲስ ቆጰሳት ሹመት እንዲያስቆሙ ጠየቀች
- የትግራይ ክልል አባቶች ለ6 ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ሰጡ
ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በሰጠው መግለጫ፤ በትግራይ ክልል በተካሄደው ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት፤ "የዶግማና የቀኖና ጥሰት" ያለው ነው በማለት በተግባሩ በእጅጉ አዝኗል ብሏል፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቷ በሰሜኑ ጦርነት በክልሉ ተቋርጦ የነበረውን መዋቅራዊ ግንኙነት ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ባለበት ወቅት፤ ፓትርያርኩ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ተብለው በሚጠሩበት ሀገረ ስብከት ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት መካሄዱ ተነግሯል።
"ጥሰቱን" አስመልክቶ ተገቢውን ውሳኔ ለመወሰን አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሀምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. መጠራቱን ሲኖደሱ ገልጿል።
ቅዱስ ሲኖዶስ በየደረጃው የቤተ ክርስቲያኗ የሰራ ኃላፊዎች እና ምዕመናን ከቤተ ክርስቲያን ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አስተላልፏል።
ምዕመናን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ ተገቢውን ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ በትግእስት እንዲጠብቁም አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ የትግራይ አባቶች የቤተክርስቲያኗን አንድነት ይሸረሽራል ካለችው የኤጲስ ቆጾሳት ሲመት እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ አሳስባ ነበር።
መንግስትም ይህን የትግራይ አባቶችን ኤጲስ ቆጾሳት የመሾም እንቅስቃሴ እንዲያደርግላት ጠይቃ ነበር።
ነገርግን የትግራይ አባቶች የቤተክርስቲያኗን ማሳሰቢያ ወደጎን በመተው በዛሬው እለት በአክሱም ለስድስት ኤጲስ ቆጾሳት ሲመት አከናውነዋል።
ይህ የትግራይ አባቶች ከቤተክርስቲያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ወደ ከፍተኛ ውጥረት ከፍ አድርጎታል።