በኢትዮጵያ በተለይም የተወሰኑ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ገደብ መጣሉን ተከትሎ የቪፒኤን ፍላጎት በ1430 በመቶ ጨምሯል
በአንድ ሀገር ያለ ኔትወርክ በብዙ ምክንያቶች መደበኛ የኔትወርክ ገደብ ሲጣል ቨርቹዋል ፕራይቬት ኔትወርክ ወይም ቪፒኤን በሚል የሚጠሩ መተግበሪያዎችን መጠቀም የተለመደ ነው።
በኢትዮጵያም መደበኛው የኔትውርክ አገልግሎት ገደብ ሲጣልበት የተለያዩ የቪፒኤን መተግበሪያዎችን ከጎግል ስቶር ላይ በማውረድ መጠቀም ተለምዷል።
በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ በተለይም የተወሰኑ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ገደብ መጣሉን ተከትሎ ተጠቃሚዎች በቪፒኤን በመጠቀም ላይ ናቸው።
አል ዐይን አማርኛ በአሁን ሰዓት በብዛት ጥቅም ላይ እየዋሉ ስላሉት ቪፒኤን መተግበሪያዎች ስለሚኖሯቸው ጥቅሞች እና ጉዳቶች ተከታዩን አዘጋጅቶላችኋል።
የቪፒኤን መተበሪያዎች ባጭሩ አንድ ሀገር ሆነን በሌላ ሀገር ኔትወርክ መጠቀም ማለት ሲሆን በተለይም የምንጠቀምበትን ሰርቨር፣ የምንጠቀማቸውን ዌብሳይቶች፣ የተጠቀምናቸወን ፋይሎች እና ሌሎች መረጃዎችን ሰዎች አልያም ስለ እኛ ማወቅ የሚፈልጉ አካላት መረጃውን ማግኘት እንዳይችሉ ያደርጋሉ።
ይሁንና ሁሉም አይነት የቪፒኤን መተግበሪያዎች አስተማማኝ ባለመሆናቸው የተወሰኑት በቀላሉ ለመረጃ መንታፊዎች ሊያፈጋልጡን ስለሚችሉ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
በአውስትራሊያ በተደረገ ጥናት 67 በመቶ የዓለማችን ቪፒኤን መተግበሪያዎች ቢያንስ አንድ መረጃ መመንተፊያ ቫይረስ ያላቸው ሲሆን ከተጠቃሚዎች የወሰዷቸውን መረጃዎች ለሶስተኛ ወገኖች አሳልፈው ይሸጣሉ።
የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከተጠቃሚዎች መረጃዎችን በመግዛት የማስታወቂያ ስራዎቻቸውን የሚያከናውኑ ሲሆን የቪፒኤን ተጠቃሚዎች ዋነኛ ኢላማ እንደሚሆኑም ተገልጿል።
በተለይም ነጻ የቪፒኤን መተግበሪያዎች ለመረጃ መንታፊዎች የተጋለጡ ሲሆኑ 65 በመቶ ነጻ የቪፒኤን መተግበሪያዎች መረጃዎችን ከተጠቃሚዎች ወስደው ለቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የሸጣሉ።
ይሁንና በክፍያ የሚገኙ የቪፒኤን መተግበሪያዎች ከመረጃ መንታፊዎች የተጠበቁ ሲሆን ደንበኞች ለመረጃዎቻቸው የሚጠነቀቁ ከሆነ የክፍያ ቪፒኤን መተግበሪያዎችን እንዲጠቀሙ ይመከራል።
በአጠቃላይ ቪፒኤን መተግበሪያዎችን መጠቀም ለመረጃ ምንተፋ፣ ለቫይረስ ጥቃት፣ ለከፍተኛ የኔትወርክ ክፍያ፣ ካለፍላጎት እና ለአሰልቺ ማስታወቂያዎች እና ለኔትወርክ መዘግየት ሊያጋልጥ ይችላል ተብሏል።
ይሁንና ቪፒኤን መተግበሪያዎች በተለይም አንድ ተጠቃሚ የሌላ ሀገር ኔትወርክ እየተጠቀመ ከሆነ በሀገሩ የተከለከሉ ነገር ግን ኔትወርኩን በሚጠቀምበት ሀገር የተፈቀዱ አገልግሎቶችን በቀላሉ ሊያስገኝ ይችላል።
ለምሳሌ ሁሉም ሀገራት የሚፈቅዷቸው እና የሚከለክሏቸው ድረገጾች፣ የቪዲዮ አምራች ኩባንያዎች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንደ ሀገራቸው ህግ የሚተዳደሩ በመሆናቸው ቪፒኤን መተግበሪያዎች በመጠቀም በሀገራቸው የተከለከሉ አገልገሎቶችን የሌላ ሀገራት ኔትወርክ በመጠቀም አገልግሎቶችን በቀላሉ ሊያስገኙልን ይችላሉ ተብሏል።