የኢራን ድሮን የሱዳኑን የእርስበእርስ ጦርነት ሁኔታ ይቀይረው ይሆን?
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እና ሚዲያው አገኘሁት ባለው የደህንነት መረጃ መሰረት የሱዳን ጦር የኢራንን ድሮን እየተጠቀመ ነው ብሏል
የሱዳን ጦር ኢራን ሰራሽ ድሮኖችን ተጠቅሞ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎችን ግስጋሴ መግታቱ እና ጦርነቱን መቀየሩ ተገልጿል
አንድ አመት ባስቆጠረው የሱዳን ጦርነት፣ የሱዳን ጦር ኢራን ሰራሽ ድሮኖችን ተጠቅሞ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎችን ግስጋሴ መግታቱን እና ጦርነቱን መቀየሩን ሮይተርስ ከፍተኛ ወታደራዊ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል
እንደዘገባው ከሆነ የሱዳን ጦር ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ የኢራን ድሮኖችን ታጥቋል።
የሱዳን ጦር ጦርነቱ በተጀመረባቸው የመጀመሪያ ወራት ያረጁ ድሮኖችን ከከባድ መሳሪያዎች ጎንለጎን ለመጠቀም ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ከፍተኛ ህዝብ በሚኖርበት ካርቱም ከተማ የመሸጉትን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በማስወጣት ብዙም ውጤታማ አልነበረም።
ጦርነቱ ከተጀመረ ከዘጠኝ ወር በኋላ ጦሩ በሰሜናዊ ካርቱም ውጤታማ የሚባል የድሮን ጥቃት ፈጽሞ ቦታዎችን ማስለቀቁ የሮይተርስ ምንጮች ጠቅሰዋል።
የሱዳን ጦር በሱዳን ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ኦምዱርማን የሚገኘውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እንቅስቃሴን፣ ምሽጋቸውን እና ከባድ መሳሪያ ያጠመዱበትን ቦታ ለመየለት ድሮን ተጠቅሟል።
ባለፉት ሳምንታት ውስጥ ጦሩ ኢላማውን የጠበቀ የድሮን ጥቃት በማድረሱ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ቦታቸውን ለቀው እንዲያፈገፉጉ አስገድዷቸዋል ተብሏል።
ጦሩ የኢራን ድሮኖች በኦምዱርማን እና በሌሎች ቦታዎች ከዚህ ቀደም ስለመጠቀሙ አልተገለጸም። ነገርግን ቡሉምበርግ እና የሱዳን መገናኛ ብዙኻን የኢራን ድሮኖች መኖራቸውን ዘግበዋል።
የኢራን ድሮኖች በቀጥታ ከኢራን መምጣታቸውን ያስተባበሉት ሮይተርስ ያናገራቸው ወታራዊ ባለስልጣን ድሮኖቹ እንዴት እንደተገዙ ወይም ጦሩ ምንያህል እንደተረከበ ከመናገር ተቆጥበዋል።
በሱዳን እና በኢራን መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው ባለፈው አመት ሲሆን ይፋዊ ወታደራዊ ግንኙነት ግን ገና በሂደት ላይ ነው።
ባለፈው አመት ኢራንን በጎበኙበት ወቅት ስለኢራን ድሮን የተጠየቁት የሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ሳድቅ "ሱዳን ከኢራን ምንም አይነት መሳሪያ አልተቀበለችም" የሚል መልስ ነበር የሰጡት።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር በኦምዱርማን ሽንፈት እንዳጋጠመው አምኗል። የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እና ሚዲያው አገኘሁት ባለው የደህንነት መረጃ መሰረት የሱዳን ጦር የኢራንን ድሮን እየተጠቀመ ነው ብሏል።
የቀጣናው እና የኢራን ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ ኢራን ሱዳንን ጦር የምትረዳው ስትራቴጂካዊ ቦታ ካለችው ሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠንከር ነው።