የሱዳን ጦር ለረመዳን ፆም ተኩስ እንደማያቆም ገለጸ
በጄነራል መሀመድ ሀምዳን ደጋሎ ወይም ሄሜቲ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር ግን በተመድ የቀረበውን የተኩስ አቁም ጥሪ መቀበሉን ገልጿል
የሱዳን ጦር ምክትል አዛዥ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር ሰላማዊ ሰዎች ከሚኖሩበት ቦታ ካለቀቀ፣ በረመዳን ወቅት ተኩስ እንደማያቆሙ ተናግረዋል
አንድ ከፍተኛ የሱዳን ጦር መሪ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር ሰላማዊ ሰዎች ከሚኖሩበት ቦታ ካለቀቀ፣ በረመዳን ወቅት ተኩስ እንደማያቆሙ ተናግረዋል።
የሱዳን ጦር ምክትል አዛዥ የሆኑት ያሲር አል አታ ይህን መግለጫ ያወጡት ጦሩ በኦምዱርማን ግዛት ቦታዎችን ማስለቀቁን ከገለጸ እና ተመድ ተኩስ እንዲቆም ከተማጸነ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
በጄነራል መሀመድ ሀምዳን ደጋሎ ወይም ሄሜቲ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር ግን በተመድ የቀረበውን የተኩስ አቁም ጥሪ መቀበሉን ገልጿል።
በሱዳን ጦር ይፋዊ የቴሌግራም ቻናል በትናንትናው እለት የተለቀቀው የአታ መግለጫ እንደገለጸው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በባለፈው ግንቦት ወር በሳኡዲ አረቢያ እና በአሜሪካ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ጦራቸውን ከሰላማዊ ሰዎች መኖሪያ የማያስወጡ ከሆነ የረመዳን ተኩስ አቁም አይኖርም።
መግለጫው ከዚህ በተጨማሪም ሄሜቲ እና ቤተሰቦቹ በሱዳን የወደፊት ፖለቲካ እና ወታደራዊ ተቋማት ውስጥ ሚና ሊኖራቸው አይገባም ብሏል።
"ስለረመዳን ተኩስ አቁም የሚያወሩ አሉ። በጦሩ እና በህዝብ የታዘዘ ተኩስ አቁም የለም" ብለዋል አታ በሰከላ ተገኝተው ወታደሮቻቸውን "እንኳን ደስ አላችሁ" ለማለት በተገኙበት ወቅት።
አጋር በነበሩት ጀነራል ሄሜቲ እና በጄነራል መካከል ጦርነት የተጀመረው በሚያዝያ 2023 ነበር።
ተመድ 25 ሚሊዮን የሚሆነው ወይም ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሱዳን ህዝብ እርዳታ እንደሚፈልግ እና ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ገልጿል።
አሜሪካ ሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች የጦር ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሳለች።
ይህን ደም አፋሳሽ ጦርነት በድርድር ለማስቆም አሜሪካ እና ሳኡዲ አረቢያ የሁለቱን ተወካዮች ማደራደር ጀምረው የነበረ ቢሆንም ያለውጤት ተቋርጧል።