የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ካርቱምን ዋና ከተማው አድርጎ መንግስት እመሰርታለሁ ሲል ዛተ
የሱዳን ልዓላዊ ም/ቤት በሀገሪቱ ባለአደራ መንግስት ያስፈልጋል ብሏል
በሀገሪቱ አስምት ወራትን በዘለቀው ጦርነት ንጹሃን የእሳት እራት እየሆኑ ነው
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ የሀገሪቱ ጦር መንግስት የሚመሰርት ከሆነ ወታደሮቻቸው በተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ተመሳሳይ እርምጃ እወስዳለሁ ሲሉ አስፈራርተዋል።
ባለፈው ወር በጦሩ መሪ ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን የሚመራው የልዓላዊ ም/ቤት ከፍተኛ ባለስልጣን በሱዳን ባለአደራ መንግስት ያስፈልጋል ብለዋል።
ሀምቲ በሚል ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አዛዥ መሀመድ ሀምዳን ዳገሎ መንግስት ለማቋቋም የሚደረግ እርምጃን በተመለከተ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
"ጦሩ መንግስት ለማቋቋም ከተነሳ እኛም በያዝናቸው ግዛቶች ካርቱምን ዋና ከተማ አድርገን ትክክለኛ ህዝባዊ መንግስት ለመመስረት እንቀሳቀሳለን" ብለዋል።
ሀምዳን ዳገሎ በቀይ ባህር በፖርት ሱዳን አካባቢ ባለአደራ መንግስት ለመመስረት የሚወሰድ እርምጃ ሀገሪቱን ለሁለት ይከፍላል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ መሀመድ ሀምዳን ዳገሎና የሱዳን ጦር መሪ ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ላለፉት አምስት ወራት እየተዋጉ ነው።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በካርቱም እና በሀሪ፣ ኦምድሩማን የመኖሪያ ሰፈሮችን ተበታትኖ የያዘ ሲሆን፤ ጦሩ ኃይሉንና ትጥቁን ተጠቅሞ ለማስወጣት በሚያደርጉት ትግል ንጹሃን የእሳት እራት እየሆኑ ነው።
በርካታ ሀገራት ሁለቱ ወገኖችን ለማሸማገል ያደረጉት ጥረት ፍሬ ሊያፈራ አልቻለም።