በሺዎች የሚቆጠሩ ሩሲያውያን ነፍሰ ጡሮች ወደ አርጀንቲና እየሄዱ ያሉት ለምንድነው?
አሁን ላይ ከሩሲያ ይልቅ የአርጀንቲና ፓስፖርት የበለጠ ነጻነት እንደሚሰጥ ይነገራል
ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ ከ5ሺህ በላይ ሩሲያውያን ነፍሰ ጡሮች ወደ አርጀንቲና ገብተዋል
ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ ከ5ሺህ በላይ ሩሲያውያን ነፍሰ ጡሮች ወደ አርጀንቲና መግባታቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አርጀንቲና ከገቡት ነፈሰ ጡር ሩሲያውያን ሴቶች 33ቱ ሐሙስ እለት የገቡ መሆናቸውም ነው የተገለጸው፡፡
የሀገሪቱ ብሔራዊ ፍልሰት ኤጀንሲ እንደገለጸው በቅቡ አርጀንቲና የገቡት ሁሉም በመጨረሻዎቹ የእርግዝና ሳምንታት ውስጥ የሚገኙ ናቸው ብሏል፡፡
ምንም እንኳን ሴቶቹ ወደ አርጀንቲና የሚመጡት ለጉብኝት እንደሆነ ቢናገሩም ፤ዋና ዓላማቸው የአርጀንቲና ዜግነት ለማግኘት ልጆቻቸው በአርጀንቲና መወለዳቸውን ማረጋገጥ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
የብሔራዊ የፍልሰት ኤጀንሲ ኃላፊ ፍሎሬንሺና ካሪናኖ እንደተናገሩት ከሆነ ነፍሰ ጡር ሴቶቹ ወደ አርጀንቲና የሚመጡት ለልጆቻቸው ዜግነት ሲሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሐሙስ እለት በአንድ በረራ ወደ አርጀንቲና ቦነስ አይረስ ከደረሱት 33 ሴቶች መካከል ሶስቱ የያዟቸው የጉዞ ሰነዶች ላይ የተገኘውን ችግር ተከትሎ የተገኘው መረጃ አመላካች መሆኑ በአብነት በማንሳት፡፡
ነፍሰ ጡር ሴቶቹ መጀመሪያ ላይ ወደ አርጀንቲና የመጡት ለጉብኝት መሆኑ ተናግረው የነበረ ቢሆንም፤ በተደረገው የማጣራት ሂደት ቱሪስት አለመሆናቸውና ለጉብኝት አንዳልመጡ አምነዋል፡፡
ሴቶች ልጆቻቸው የአርጀንቲና ዜግነት እንዲኖራቸው የፈለጉበት ምክንያት ከሩሲያ ፓስፖርት በበለጠም ነጻነት ስለሚሰጥ ነውም ነው የተባለው፡፡
"ችግሩ ወደ አርጀንቲና በመምጣት ልጆቻቸውን እንደ አርጀንቲናዊ አስመዝግበው መውጣታቸው ነው። ፓስፖርታችን በዓለም ዙሪያ በጣም ደህንነቱ የተጠበቀ ነው። [የአርጀንቲና ፓስፖርት የያዙ] ወደ 171 ሀገሮች ከቪዛ ነጻ እንዲገቡ ያስችላቸዋል" ሲሉም ነው የተናገሩት የብሔራዊ የፍልሰት ኤጀንሲ ኃላፊዋ ፍሎሬንሺና ካሪናኖ ፡፡
ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችውን ወታደራዊ ዘመቻ ተከትሎ በተጣለባት የቪዛ ገደብ ምክንያት ሩሲያውያን አሁን ላይ ከቪዛ ነጻ መጓዝ የሚችሉት ወደ 87 ሀገራት ብቻ መሆኑ ይታወቃል፡፡