አርጀንቲና ከአለም ጤና ድርጅት አባልነት ለመውጣት ወሰነች
ሀገሪቱ በዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የሚመራው ተቋም በተወሰኑ ሀገራት ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ስር ወድቆ ገለልተኛ መሆን ተቸግሯል ብላለች
የደቡብ አሜሪካዋ ሀገር ለአለም ጤና ድርጅት በየአመቱ 8 ሚሊየን ዶላር ታዋጣለች
የአርጀንቲናው ፕሬዝዳንት ሃቪየር ሚሌይ ሀገራቸው ከአለም ጤና ድርጅት አባልነት እንድትወጣ አዘዋል።
ፕሬዝዳንቱ የወዳጃቸውን ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ በመከተል ሀገራቸውን ከአለም ጤና ድርጅት ለማስወጣት በቀጣይ ቀናት ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ይፈርማሉ ተብሏል።
የፕሬዝዳንት ሚሌይ ቃል አቀባይ ማኑኤል አዶርኒ በቦነስ አይረስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አርጀንቲና ከድርጅቱ የምትወጣው "በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት በታዩ ጥልቅ የጤና አስተዳደር ልዩነቶች" ምክንያት ነው ብለዋል።
በወረርሽኙ ወቅት የድርጁቱ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች "በሰው ልጅ ታሪክ ትልቁን መዘጋት" (ከቤት ያለመውጣት) ማስከተሉን ጠቅሰዋል።
ሚሎይ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት የቀድሞው ፕሬዝዳንት አልቤርቶ ፈርናንዴዝ ያሳለፏቸው የእንቅስቃሴ ገደቦች የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ ይጎዳል፤ መንግስት ወረርሽኙን እንደ "ማፈኛ" ተጠቅሞበታል በማለት በተደጋጋሚ ሲወቅሱ እንደነበር ይታወሳል።
ቃልአቀባያቸው ማኑኤል አዶርኒ በመግለጫቸው የአለም ጤና ድርጅት ስማቸውን ባልጠቀሷቸው ሀገራት ተጽዕኖ ስር በመውደቁ ገለልተኛ መሆን እንዳልቻለ አንስተዋል። አሜሪካ ከድርጅቱ አባልነት ለመልቀቅ ስትወስን ድርጅቱ በቻይና ተጽዕኖ ስር ወድቋል ማለቷ አይዘነጋም።
"ለጤና እምብዛም የማይሰሩ" አለማቀፍ ተቋማት በሉአላዊነታችን ላይ ጣልቃ እንዲገቡ አንፈቅድም ማለታቸውንም አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ሚሌይ ባለፈው አመት ወረርሽኞችን በአለም ጤና ድርጅት ማዕቀፍ ለማስተዳደር የቀረበውን ስምምነት ሉአላዊነትን ይዳፈራል በሚል አልፈርምም ማለታቸው ይታወሳል።
የአለም ጤና ድርጅት የአርጀንቲና ውሳኔን እያጤነ መሆኑን ከመግለጽ ውጪ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጠም።
የደቡብ አሜሪካዋ ሀገር ለአለም ጤና ድርጅት 8 ሚሊየን ዶላር ታዋጣለች። አሜሪካ በአንጻሩ በ2024 ብቻ 950 ሚሊዮን ዶላር ገደማ በማዋጣት ከፍተኛውን ድርሻ ይዛለች።
የዋሽንግተን ከድርጅቱ አባልነት መልቀቅ ከፍተኛ ተጽዕኖ ቢኖረውም የአርጀንቲና መዋጮ አነስተኛ እንደመሆኑ እምብዛም ለውጥ ይፈጥራል ተብሎ አይጠበቅም።