ቻይና በአንጻሩ በሁለት አመት ውስጥ ለአለም ጤና ድርጅት ያዋጣችው 157 ሚሊየን ዶላር ብቻ ነው ተብሏል
ከአራት አመት ተኩል በፊት አሜሪካን ከአለም ጤና ድርጅት ለማስወጣት የሞከሩት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ዋይትሃውስ እንደገቡ የቀደመ ጥረታቸውን ለማሳካት ውሳኔ አሳልፈዋል።
በባይደን አስተዳደር ሳይፈጸም የቀረውን ዋሽንግተንን ከአለም የጤና ድርጅት የማስወጣት ሂደት እውን ለማድረግ የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
የአለም ጤና ድርጅት "የኮቪድ 19 ወረርሽኝን በሚገባ አልተቆጣጠረም፤ ቻይና አለምን እንድታሳስት ረድቷል" የሚሉት ትራምፕ፥ ድርጅቱ ፈጣን ሪፎርም ማድረግና ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት ነጻ መሆን አልቻለም ሲሉ ይከሱታል።
የድርጅቱ አባል ሀገራት በተለይ ቻይና የሚያዋጡት አመታዊ ክፍያ ፍትሃዊነት የሌለው መሆኑን በመጥቀስም ሀገራቸው ከድርጅቱ አባልነት እንድትወጣ ወስነዋል።
አሜሪካ ለአለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ ገንዘብ በማዋጣት ቀዳሚ ናት። ድርጅቱ በቅርቡ ባወጣው መረጃ ዋሽንግተን በ2022 እና 2023 ለድርጅቱ 1.28 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ አድርጋለች። 1.02 ቢሊየን ዶላሩ በበጎፈቃደኝነት ያዋጣችው ሲሆን 47 ሚሊየን ዶላሩ ለአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ የሰጠችው ነው።
ቻይና በአንጻሩ በተመሳሳይ ወቅት ለድርጅቱ የሰጠችው 157 ሚሊየን ዶላር ብቻ ነው ይላል ስታስቲካ ያወጣው መረጃ።
የአለም ጤና ድርጅት ለ2022 እና 2023 ካጸደቀው የ10.4 ቢሊየን ዶላር በጀት ውስጥ የአሜሪካ ድርሻ 12 በመቶ ሲሆን፥ ከታየው የ2 ቢሊየን በጀት ጉድለት አንጻር ሲታይ የሀገሪቱ ድርሻ ወደ 15 በመቶ ከፍ እንደሚልም ተመላክቷል።
በትራምፕ ውሳኔ ማዘኑን ያስታወቀው ድርጅቱ ወጪውን ለመቀነስ ማቀዱን ይፋ አድርጓል።
ለአለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ ድጋፍ የሚያደርጉ ሀገራትና ተቋማትን ይመልከቱ፦