የአለም ጤና ድርጅት የአሜሪካን መውጣት ተከትሎ የወጭ ቅነሳ ሊያደርግ እንደሆነ ተገለጸ
ትራምፕ በ2020 በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው ድርጅቱ "ቻይና አለምን እንድታሳስት ረድቷል" በማለት ነበር ከድርጅቱ ለመውጣት እርምጃ መውሰድ የጀመሩት
አሜሪካ የአለም ጤና ድርጅትን አጠቃላይ በጀት 18 በመቶ መሸፈን እስካሁን ከፍተኛ ገንዘብ ከሚያዋጡ ሀገራት ውስጥ ቀዳሚ ነች
የአለም ጤና ድርጅት የአሜሪካን መውጣት ተከትሎ የወጭ ቅነሳ ሊያደርግ እንደሆነ ተገለጸ።
የአለም ጤና ደርጅት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ከድርጅቱ እንድትወጣ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ ወጭ እንደሚቀንስ እና የትኛው የጤና መርሃግብር ቅድሚያ እንደሚሰጠው እንደሚገመግም የድርጅቱ ኃላፊ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ለውስጥ ሰራተኞች መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የአለም ጤና ድርጅት ቃል አቀባይ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም የወጭ ቅነሳ ውሳኔው ትክክል መሆኑን ማረጋገጣቸው ዘገባው ጠቅሷል።
የተባበሩት መንግስት ድርጅት(ተመድ) አሜሪካ በ1948ቱ የአሜሪካ ኮንግረስ ውሳኔ መሰረት ከአንድ አመት ማስጠንቀቂያ በኋላ በጥር 22፣2026 ከአለም ጤና ድርጅት እንደምትወጣ አረጋግጠዋል።
የውሳኔ ሀሳቡ ዋሽንግተን ከመውጣቷ በፊት እዳዋን መክፈል እንዳለባትም ያስገድላል።
አሜሪካ የአለም ጤና ድርጅትን አጠቃላይ በጀት 18 በመቶ መሸፈን እስካሁን ከፍተኛ ገንዘብ ከሚያዋጡ ሀገራት ውስጥ ቀዳሚ ነች። የድርጁቱ 2024-2025 በጀት 6.8 ቢሊዮን ዶላር ነበር። አሜሪካ ከአመት በፊት መከፈል የነበረበትን የ130 ሚሊዮን ዶላር የአባላት መዋጮ በጥር 2024 መክፈሏን የአለም ጤና ድርጁት ቃል አቀባይ ክርስቲያን ሌንድሚር ባለፈው አርብ እለት በጄኔቫ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ አክለው እንደገለጹት "አሁን መክፈል ያለበትን የአባልነት መዋጮንና የ2025 ግምገማን አልተቀበልንም" ብለዋል። አሜሪካ ለድርጅቱ የምታደርገው መዋጮ የበጎፈቃድ ክፍያን፣ ለተለዩ ፕሮግራሞች የምታደርገውን ክፍያና በማንኛውም ሰአት ሊቆም የሚችሉ ክፍያዎችን ያካትታል።
እንዘገባው ከሆነ ድርጅቱ አባል ሀገራት የሚከፍሉትን መዋጮ እንዲጨምሩና ወጭ ለመቀነስ የሚያሰችሉ እርምጃዎችን እንደሚወሰድ ለሰራተኞች ግልጽ አድርጓል።
የድርጅቱ ወጭ ቀነሳ የተለየ ፍቃድ ሳያስፈልጋቸው ስብሰባዎችን በበይነ መረብ ማድረግን፣ የአይቲ እቃዎችን መተካትንና ከደህንነት ጋር የተገናኙ ካልሆነ በስተቀር ወይም ቀድሞ ካልጸደቀ የቢሮ እድሳትን ማስቀረትን ያካትታል።
ድርጅቱ ተጨማሪ የወጭ ቅነሳ እርምጃዎችን እንደሚያሳወቅ ገልጿል።
የትራምፕ ከአለም ጤና ድርጅት መውጣት የማይጠበቅ አይደለም። ትራምፕ በ2020 በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው ድርጅቱ "ቻይና አለምን እንድታሳስት ረድቷል" በማለት ነበር ከድርጅቱ ለመውጣት እርምጃ መውሰድ የጀመሩት።
የአምጤና ድርጅት ግን የትራምፕን ክስ አስተባብሎ፣ ቻይና መረጃውን ለአለም እንድታጋራ ጫና ማድረጉን እንደሚቀጥል መግለጹ ይታወሳል።