አርጀንቲና ከክሮሽያ የአለም ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ተጠባቂ ጨዋታ
የሊዮኔል ሜሲ ሀገር በምድብ የመጀመሪያ ጨዋታ በሳኡዲ አረቢያ ከገጠማት ሽንፈት አገግማ ለግማሽ ፍጻሜው ደርሳለች
ተጋጣሚዋ ክሮሺያም ብራዚልን በመለያ ምት በመርታት ግማሽ ፍጻሜውን መቀላቀሏ ይታወሳል
የኳታር የአለም ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ ይደረጋሉ።
ዛሬ ምሽት 4 ስአት ከ80 ሺህ በላይ ተመልካቾችን መያዝ በሚችለው ሉሳይል ስታዲየም አርጀንቲና ከክሮሽያ ይፋለማሉ።
አርጀንቲና በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ በሳኡዲ አርቢያ 2 ለ 1 ስትሸነፍ የኳታር ቆይታዋ ሊያጥር እንደሚችል ተገምቶ ነበር።
ይሁን እንጂ የምድብ እና ጥሎ ማለፍ ጨዋታዎችን እያሸነፈች ኔዘርላንድስንም በመለያ ምት አሸንፋ ለግማሽ ፍጻሜው ደርሳለች።
4 ሚሊየን ህዝብ ያላት ክሮሽያም በመለያ ምቶች ጃፓንን ከሩብ ፍጻሜው፤ ብራዚልን ደግሞ ከግማሽ ፍጻሜው ውጭ ማድረጓ ይታወሳል።
የሰባት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው ሊዮኔል ሜሲ ከ2014 ወዲህ ሁለተኛውን የፍጻሜ ጨዋታ ለማድረግ ነው ወደ ሜዳ የሚገባው።
ውሃ ሰማያዊ እና ነጭ ለባሾቹ ለስድስተኛ ጊዜ ለፍጻሜ ለመድረስ ክሮሽያን የሚገጥሙ ሲሆን፥ ለግማሽ ፍጻሜ ደርሰው ተሸንፈው አያውቁም።
ይሁን እንጂ አርጀንቲና ከአውሮፓ ሀገራት ጋር ካደረገቻቸው ሰባት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለችው አንዱንን ብቻ ነው።
የ35 አመቱ ሜሲ በአምስተኛ የአለም ዋንጫ ተሳትፎው ሀገሩን ከ1986 ወዲህ ሻምፒዮን ለማድረግ ትልቅ ሃላፊነት አለበት።
ክሮሺያዊው ሉካ ሞድሪችም ሀገሩን ከጣሊያን፡ ኔዘርላንድስ እና ጀርመን በመቀጠል በተከታታይ ለአለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታዎች የደረሰች ለማድረግ ይፋለማል።
አርጀንቲና እና ክሮሽያ እስካሁን አምስት ጊዜ ተገናኝተው ሁለት ሁለት ጊዜ ተሸናንፈዋል፤ በአንዱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
ስድስተኛው (በአለም ዋንጫው ሶስተኛው) ፍልሚያቸው ምሽት 4 ስአት ሲደረግ ማን ድል ያደርግና ለፍጻሜ ይደርስ ይሆን?