5 ቢሊየን የሚጠጉ ሰዎች የአለም ዋንጫውን ተመልክተውታል - ኢንፋንቲኖ
ከ3 ነጥብ 27 ሚሊየን በላይ ተመልካቾችም በስታዲየሞች ጨዋታዎቹን መከታተላቸውን የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በዶሃ በሰጡት መግለጫ አንስተዋል።
ያለምንም መጥፎ አጋጣሚ የተካሄደው የኳታር የአለም ዋንጫ እጅግ አስደሳች እና የእግርኳስን አለማቀፋዊነት ያሳየ ስለመሆኑም አብራርተዋል
የኳታሩን የአለም ዋንጫ በአለም ዙሪያ 5 ቢሊየን ሰዎች ተመልክተውታል አሉ የአለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ።
ኢንፋንቲኖ በዶሃ በሰጡት መግለጫ ከ3 ነጥብ 27 ሚሊየን በላይ ተመልካቾችም በስታዲየሞች ጨዋታዎቹን መከታተላቸውን ነው ያነሱት።
ጨዋታዎቹ ያለምንም ፈታኝ ሁኔታ መካሄዳቸው እጅግ አስደሳች ነው ያሉት ኢንፋንቲኖ ፥ መግለጫቸውን ያማረ የአለም ዋንጫ ያዘጋጀችውን ኳታር በማመስገን ነው።
ኳታር “እግርኳስ በርግጥም አለማቀፋዊ መሆኑን አሳይታለች” ነው ያሉት ኢንፋንቲኖ።
ለዚህም አፍሪካዊቷ ሞሮኮ ለግማሽ ፍጻሜ መድረሷንና የአለም ዋንጫው የመጀመሪያዋ የሴት ዳኛ (ስቴፋኒ ፍራክፓርት ) በኳታር መዳኘታቸውን እንደ ማሳያ አንስተዋል።
የፊፋው ፕሬዚዳንት አያይዘውም የማህበሩን ምክር ቤት ስብስባና የቀጣይ እቅዶች አብራርተዋል በመግለጫቸው።
ባለፉት አራት አመታት ፊታ 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ትርፍ ማግኝቱን በመጥቀስም ለቀጣይ አራት አመታት የ11 ቢሊየን ዶላር በጀት መያዙን ገልጸዋል።
ከዚህ በጀት ውስጥ 10 ቢሊየን ዶላሩ ለእግር ኳስ ልማት እንደሚውልም ነው የጠቆሙት።
የአለም የክለቦች ዋንጫ የአለም ዋንጫውን አይነት ቅርጽ ይዞ እንዲካሄድ መታሰቡን ያነሱት ኢንፋንቲኖ፥
ሞሮኮ የ2023ቱን የክለቦች የአለም ዋንጫ እንድታካሂድ መመርጧን አረጋግጠዋል።
ፊፋ አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጋራ በሚያዘጋጁት የ2026ቱ የአለም ዋንጫ ላይ አዲስ ፎርማት ሊከተል እንደሚችል ፍንጭ ስጥተዋል።
ሶስት ሀገራትን የሚይዙ 16 ቡድኖች እንዲኖሩ በማድረግ ሁለቱ ወደ ጥሎ ማለፉ እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ነው የታሰበው።
ነገር ግን ምክክር ተደርጎበት የመጨረሻ ውሳኔ አላገኘም ብለዋል።
ፊፋ የአለም ዋንጫውን ተሳታፊዎች ቁጥር ከ32 ወደ 48 እንደሚያሳድግ መግለጹ ይታወሳል።