ድሉን ተከትሎ ሜሲ በ2026ቱ የአለም ዋንጫ ሊሳተፍ እንደሚችል እየተነገረ ነው
በአሜሪካ አዘጋጅነት የተካሄደው የደቡብ አሜሪካ ሀገራት አህጉራዊ የእግርኳስ መድረክ (ኮፓ አሜሪካ) በአርጀንቲና አሸናፊነት ተደምድሟል።
በሚያሚ ሃርድ ሮክ ስታዲየም ኮሎምቢያን የገጠመችው አርጀንቲና ላውታሮ ማርቲኔዝ በጭማሪ ስአት (112ኛ ደቂቃ) ላይ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል በማሸነፍ 16ኛ የኮፓ አሜሪካ ዋንጫዋን አንስታለች።
ከስታዲየሙ ውጭ በተፈጠረ ግርግር ለ80 ደቂቃዎች በተራዘመው የፍጻሜ ጨዋታ አጋማሽ ኮሎምቢያዊቷ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ሻኪራ ስራዎቿን አቅርባለች።
የኮሎምቢያው አሰልጣኝ አርጀንቲናዊው ኔስቶር ሎሬንዞ የሻኪራ ሙዚቃ ሁለተኛው አጋማሽ ከ25 ደቂቃዎች በኋላ እንዲጀመር በማድረጉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ያለግብ ተጠናቆ ወደ ጭማሪ ስአት ያመሩት አርጀንቲና እና ኮሎምቢያ ወደ ፍጹም ቅጣት ምት ሊያመሩ ነው ተብሎ ሲጠበቅ ላውታሮ ማርቲኔዝ ሀገሩን ለድል አብቅቷል።
በውድድሩ አምስት ጎሎችን ያስቆጠረው ማርቲኔዝ የወርቅ ጫማ ተሸላሚ ሆኗል።
አርጀንቲናው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ በኮፓ አሜሪካ የተጠበቀውን ያህል ውጤታማ ባይሆንም ሁለተኛ የኮፓ አሜሪካ ዋንጫውን አሳክቷል።
እስከ34 አመቱ በአለማቀፍ ውድድሮች ዋንጫ ያላነሳው ሜሲ፥ ከ2021 ወዲህ ሶስት ዋንጫዎችን ከሀገሩ ጋር አሳክቷል (ሁለት ኮፓ አሜሪካ እና አንድ የአለም ዋንጫ)።
የ37 አመቱ አጥቂ በዘንድሮው ኮፓ አሜሪካ በግማሽ ፍጻሜ በካናዳ ላይ ነው ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው። በሩብ ፍጻሜው ከኢኳዶር ጋር በመለያ ምት ሲያሸንፉም መሳቱ አይዘነጋም።
ከክለቡ ኢንተርሚያሚ በቅርብ ርቀት የተካሄደው የፍጻሜ ጨዋታ በድል መጠናቀቁ ተከትሎ ተጫዋቹ አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጋራ በሚያዘጋጁት የ2026ቱ የአለም ዋንጫ ነጭና ውሃ ሰማያዊ ለባሾቹን ሊቀላቀል እንደሚችል ተገምቷል።
በ28 ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ጉዞዋ በአርጀንቲና የተገታው ኮሎምቢያ ብቸኛ የኮፓ አሜሪካ ዋንጫዋ በ2001 ራሷ ባዘጋጀችው ውድድር ያነሳችው ነው።