በኮፓ አሜሪካ ኮሎምቢያ ኡራጋይን በማሸነፍ ለፍጻሜ ደረሰች
ከ23 አመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ለፍጻሜ የደረሰችው ሀገር በመጪው እሁድ ከአርጄንቲና ጋር ለዋንጫው ትፋለማለች
ከፍተኛ ውጥረት በነበረበት ጨዋታ አንድ ቀይ እና 7 ቢጫ ካርዶች ተመዘዋል
በኮፓ አሜሪካ ኮሎምቢያ ኡራጋይን በማሸነፍ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ ለፍጻሜ መድረስ ችላለች።
ትናንት ሌሊት በተደረገው ጨዋታ ኡራጋይን አንድ ለዜሮ በሆነ ውጤት መርታት የቻለው የኮሎምቢያ ብሄራዊ ቡድን በመጪው እሁድ በፍጻሜው ጨዋታ የሜሲን ሀገር አርጄንቲናን ይገጥማል።
ጄፈርሰን ሊርማ በ39ኛው ደቂቃ ያስቆጣራት ግብ ከ2001 በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ብሔራዊ ቡድኑን ለፍጻሜ አብቅታለች።
ሀይል በተቀላቀለበት እና ጥፋቶች በበዙበት ጨዋታ አንድ ተጫዋች በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣባት ኡራጋይ በ69 በመቶ ኳስ ቁጥጥር የጨዋታውን ብልጫ መውሰድ ብትችልም ድል ሳይቀናት ቀርቷል።
ከፍተኛ ውጥረት እና ሀይል በተቀላቀለበት ጨዋታ አንድ ቀይ እና 7 ቢጫ ካርዶች ተመዘዋል።
ጨዋታው ከተገባደደ በኋላ ዳርዊን ኑኑዝ እና የኡራጋይ የቡድን አጋሮቹ ከኮሎምብያ ደጋፊዎች ጋር የተጋጩ ሲሆን ኑኑዝ በአንድ የኮሎምቢያ ደጋፊ ላይ ቡጢ ሲሰነዝር ታይቷል።
ከ2021ዱ የኮፓ አሜሪካ አሸናፊ አርጄንቲና ጋር በመጪው እሁድ የሚገጥሙት ኮሎምቢያዎች ቀላል ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብሎ አይጠበቅም።
በውድድሩ ደማቅ ታሪክ ብርቱ የውድድር ክብረወሰን ያላት አርጀንቲኒ 15 የኮፓ አሜሪካ ዋንጫዎችን ያነሳች ሲሆን ስድስት ጊዜ ደግሞ ለዋንጫ ፍልሚያ ቀርባለች።
አርጄንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ለብሄራዊ ቡድን በሚያደርገው የመጨረሻ ጨዋታ ዋንጫውን የማንሳት ጽኑ ፍላጎት አለው።
ማክሰኞ እለት በተካሄደው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ አርጄንቲና ካናዳን 2-0 ስታሸንፍ ሜሲ አንድ ግብ ማስቆጠር ችሏል።
የኮሎምቢያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኔስተር ሎሬንዞ በበኩላቸው ተጨዋቾቻችን ከፍተኛ የዋንጫ ርሀብ አለባቸው በፍጻሜ ጨዋታው የምንገጥመው የአርጄንቲና ብሔራዊ ቡድን ከባድ ተፎካካሪ እንደሆነ እናውቃለን ነገር ግን ዋንጫውን ለመውሰድ ነው እዚህ የመጣነው ብለዋል።