በአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ስፔን እንግሊዝን በመርታት የ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ሻምፒዮን መሆን ችላለች
ለአንድ ወር ያህል የተካሄደው የ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡
በአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ስፔን እንግሊዝን በመርታት የ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ሻምፒዮን መሆን ችላለች።
የስፔን ብሔራዊ ቡድን የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንን 2ለ1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ነው የ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ሻምፒዮን የሆነው።
ለስፔን ብሔራዊ ቡድን የማሸነፊያ ግቦችን ኒኮ ዊሊያምስ እና ሚኬል ኦያርዛባል ከመረብ ማሳረፍ የቻሉ ሲሆን፤ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንን ከሽንፈት ያልታደገች ግብ ኮል ፓልመር ማስቆጠር ችሏል።
በዘንድሮ የአውሮፓ ዋንጫ ውድድር ላይ የ17 ዓመቱ ስፔናዊ ላሚን ያማል ምርጥ ወጣት ተጨዋች በመሆን ተሸላሚ ሆኗል።
የስፔን የመሐል ሜዳ ተጨዋች ሮድሪ የዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ ውድድር ምርጥ ተጨዋች በመሆን መመረጡ ይፋ ሆኗል።
በውድድሩ ጠንካራ ቡድን መስርተው ምንም ጨዋታ ሳይሸነፉ ለዋንጫ የደረሱት ስፔኖች የእንግሊዝን ለ60 አመታት የቆየ የዋንጫ ርሀብ ለማስታገስ አልፈቀዱም።
ሃገራቱ ከዚህ ቀደም በአለም አቀፍ ውድድሮች 27 ጊዜ ተገናኝተው ስፔን 11 ጊዜ ስታሸንፍ እንግሊዝ 13 ጊዜ አሸንፋለች፤ 4 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
የሶስቱ አናብስት አሰልጣኝ ጋሬዝ ሳውዝጌት በውድድሩ ታሪክ ሁለት የአውሮፓ ዋንጫ ፍፃሜ የተሸነፉ የመጀመሪያው አሰልጣኝ ሆነዋል።
የብሄራዊ ቡድኑ አምበል ሃሪ ኬን በፍፃሜው የገጠማቸው ሽንፈት ሀዘኑ ከባድ መሆኑን ከጨዋታው በኋላ በሰጠው አስተያየት ገልጿል።
“ በፍፃሜ መሸነፍ በጣም ከባድ ነው “ ሲል የገለፀው ሀሪ ኬን ጥሩ ተጫውተናል የአቻነት ግብ አስቆጥረን ወደ ጨዋታው ተመልሰንም ነበር ነገርግን ልንጠቀምበት አልቻልንም " ሲል ተናግሯል።