"አሪያን 6" - የአውሮፓውያን ከአሜሪካ "ነጻ መውጫ" ተስፋ
ፈረንሳይ በአውሮፓውያኑ "አሪያን 6" ሮኬት የስለላ ምስሎችን የምትልክ የስለላ ሳተላይት አስወንጭፋለች

የኤለን መስኩ ስፔስኤክስ በበኩሉ የአለማችን ግዙፉን ሮኬት ለማስወንጨፍ ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል
የአውሮፓ ስፔስ ተቋም ሮኬት "አሪያን 6" በትናንትናው እለት የመጀመሪያ የተሳካ ተልዕኮ ፈጽማለች።
የፈረንሳይ የስለላ ሳተላይትን የተሸከመችው ሮኬት በደቡብ አሜሪካ ከምትገኘው የፈረንሳይ ግዛት "ፍሬንች ጉይና" በመወንጨፍ ከምድር 800 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ሳተላይቷን ማሳረፍ ችላለች ተብሏል።
በአዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የደህንነት ዋስትና ላይ ጥርጣሬ የገባቸው አውሮፓውያን ከአሜሪካ "ጥገኝነት" ለመላቀቅ መስራት እንዳለባቸው ተስማምተዋል።
የ"አሪያን 6" ሮኬት ስኬታማ ተልዕኮ ሩሲያ ከዩክሬኑ ጦርነት መጀመር በኋላ ግዙፍ "ሶዩዝ" ሮኬቷን ማንቀሳቀሷን ተከትሎ አውሮፓውያን በነጻነት ትልልቅ ሳተላይቶችን በምድር ምህዋር ላይ ማስገባት እንደሚችሉ ያረጋገጠ ነው ተብሏል።
አውሮፓውያን ከፈረንጆቹ 2020 ጀምሮ ሮኬቷን ለማስወንጨፍ ቢያስቡም በተለያዩ ምክንያቶች ሲራዘም መቆየቱን ፍራንስ 24 አስታውሷል።
"ሲኤስኦ-3" የተሰኘችው የፈረንሳይ የስለላ ሳተላይት በ2018 እና 2020 ከመጠቁ ሌሎች የሀገሪቱ ሳተላይቶች ጋር በመተሳሰር ወቅታዊ ምስሎችን በፍጥነት ታቀብላለች ተብሎ ይጠበቃል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለዩክሬን ከሳተላይት የሚገኙ የደህንነት መረጃዎችን አላጋራም ማለቱ አውሮፓውያኑ በስፔስ የተያዘባቸውን የበላይነት ዳግም እንዲያጤኑት አድርጓል።
የፈረንሳዩ የመከላከያ ሚኒስትር ሰባስቲያን ሌኮርኑ "አውሮፓውያን በፍጥነት ሊነቁባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች አንዱ ስፔስ (ጠፈር) ነው" ብለዋል።
ከአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ወታደራዊ ሳተላይቶችን ያመጠቁት ፈረንሳይ እና ጣሊያን ብቻ ናቸው። ሀገራቱ 10 (እኩል አምስት አምስት) የስለላ ሳተላይቶች አሏቸው።
አሜሪካ እና ቻይና በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደራዊ ሳተላይቶች አሏቸው የሚሉት "የስፔስ አብዮት" መጽሃፍ ደራሲ ፍሊፕ ስቴንገር፥ አውሮፓ ወደኋላ የቀረችበትን ጉዳይ ልታስብበት ይገባል ብለዋል።
በ"አሪያን 6" ሮኬት በየአመቱ 12 ሳተላይቶችን ማምጠቅ እንደሚገባ የፈረንሳይ ባለስልጣናት እየተናገሩ ነው።
በሌላ በኩል የአውሮፓውያኑን የስፔስ ኢንዱስትሪ በብርቱ የፈተነው የኤለን መስኩ ስፔስኤክስ በትናንትናው እለት በቴክሳስ የአለማችን ግዙፉን ሮኬት ለማስወንጨፍ ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።
123 ሜትር ከፍታ ያለው ሮኬት እንደተወነጨፈ የፈነዳ ሲሆን፥ ያደረሰው ጉዳት ስለመኖሩ እስካሁን የተገለጸ ነገር የለም። የስፔስኤክስ ግዙፉ ሮኬት ሙከራ ሳይሳካ ሲቀር የትናንቱ በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።