ማክሮን የአውሮፓ ሀገራትን የአለም ጦርነት ገደል ውስጥ ለመክተት እየገፋ ነው - ሩሲያ
የፈረንሳይና ብሪታንያ መሪዎች ከሰሞኑ እየሰጡት ያለው አስተያየት በጠንካራ ወታደራዊ አቅም የሚደገፍ ባለመሆኑ የትም እንደማይደርስ ነው የክሬምሊን ባለስልጣናት ያስታወቁት

የትራምፕ አስተዳደር አውሮፓ ለደህንነቷ አሜሪካ ላይ መተማመን እንደማትችል ማሳየቱ የአውሮፓ መሪዎችን ስጋት ላይ ጥሏል
ሩሲያ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የአውሮፓ ሀገራትን የአለም ጦርነት ገደል ውስጥ ለመክተት እየገፋ ነው ስትል ከሰሰች።
ሞስኮ የአውሮፓ ስጋት ሆናለች ያሉት ማክሮን ፓሪስ "በታሪክ እጥፋት" የምትገኘውን አውሮፓ በኒዩክሌር መሳሪያዎቿ ጋሻ ሆና ለመጠበቅ ዝግጁ መሆኗንም ለህዝብ ባስተላለፉት መልዕክት ተናግረዋል።
የዩክሬኑ ጦርነት ወደ "አለማቀፍ ግጭት" መቀየሩን በመጥቀስ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፊት ለተነሳችው ኬቭ የተጠናከረ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል።
ትራምፕ ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ግንኙነታቸውን ለማደስ መፈለጋቸው አውሮፓ ለደህንነቷ አሜሪካ ላይ መተማመን እንደማትችል ማሳየቱን የሚጠቅሱ የአውሮፓ መሪዎች ከሰሞኑ ተከታታይ ምክክር እያደረጉ ይገኛሉ።
የሩሲያ ባለስልጣናት በተለይ ከፈረንሳይ እና ብሪታንያ መሪዎች የሚሰነዘሩ አስተያየቶች ሲያጣጥሉ ሰንብተዋል።
ለማክሮን የትናንት ንግግር ምላሽ የሰጡት የሩሲያ ሴናተር ኮንስታንቲን ኮሳቼቭ "ማክሮን በተሳሳተ መነሻ ከፍተኛ ስህተት ያለበት ድምዳሜ ላይ ደርሷል፤ ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት የጀመረችው የአሜሪካ መራሹ ኔቶ ወደ ሩሲያ መስፋፋትን ለማስቆም እንደሆነ ግልጽ ነው" ብለዋል።
"ሩሲያውያን መጡላችሁ" በሚል ማክሮን ለዜጎቻቸውና ለአውሮፓውያን እያስተላለፉት ያለው መልዕክት ምዕራባውያንን ለአዲስ የአለም ጦርነት የሚያነሳሳ መሆኑንም አብራርተዋል።
የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ደግሞ ማክሮንን "ማይክሮን" የሚል የስላቅ ስያሜ ሰጥተው በ2027 ከስልጣናቸው ይነሳሉ፤ ምንም ስጋት አይፈጥሩም ማለታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
የክሬምሊን ባለስልጣናት ከሰሞኑ ከማክሮን ብሎም ከብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታመር የሚደመጡ የጦርነት ጉሰማ አስተያየቶች በጠንካራ ወታደራዊ አቅም የሚደገፍ አለመሆኑንና ሩሲያ በዩክሬን የምታደርገውን ግስጋሴ እንደማያስቆም ተናግረዋል።
ሩሲያ እና አሜሪካ የአለማችን ቀዳሚዎቹ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት ሀገራት ናቸው፤ እያንዳንዳቸው ከ5 ሺህ በላይ የኒዩክሌር አረር ያላቸው ሲሆን ከአለም ሀገራት የ88 በመቶውን ድርሻ ይይዛሉ።
ቻይና በ500 ትከተላለች፤ ፈረንሳይ እና ብሪታንያ በአንጻሩ ከሞስኮ በብዙ እጥፍ ዝቅ ያለ አቅም ነው ያላቸው። ፓሪስ 290፤ ለንደን ደግሞ 225 የኒዩክሌር አረር እንዳላቸው የአሜሪካ የሳይንቲስቶች ማህበር (ፋስ) መረጃ ያሳያል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ባለፈው አመት መደበኛው የሩሲያ ጦር ቁጥር በ180 ሺህ እንዲያድግ መወሰናቸው ይታወሳል። ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ወታደሮች ያሉት የሩሲያ ጦር በሰራዊት ብዛት ከቻይና በመቀጠል ከአለም ሁለተኛው ነው።