የአውሮፓ ህብረት የሩሲያን ነዳጅ መግዛት አቆማለሁ በሚል ያስቀመጠውን ውሳኔ አራዘመ
ህብረቱ ከ2027 በኋላ የሩሲያን ነዳጅ መግዛት አቆማለሁ የሚል ጊዜ ገደብ አስቀምጦ ነበር

የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ነዳጅ ለይ ማዕቀብ የጣለ ቢሆንም በርካታ ሀገራት አሁንም ከሞስኮ ነዳጅ ይሸምታሉ
የአውሮፓ ህብረት የሩሲያን ነዳጅ መግዛት አቆማለሁ በሚል ያስቀመጠውን ውሳኔ አራዘመ፡፡
ከሶስት ዓመት በፊት ሩሲያ ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ ልዩ ዘመቻ በሚል ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን መላኳን ተከትሎ ነበር በአውሮፓ ጦርነት የተቀሰቀሰው፡፡
ሶስተኛ ዓመቱን በቅርቡ የደፈነው ይህ ጦርነት እንዲቆም የኔቶ አባል ሀገራት በሩሲያ ላይ ከ20 ሺህ በላይ ማዕቀቦችን ጥለዋል፡፡
ከነዚህ ማዕቀቦቹ መካከልም ሩሲያ ነዳጇን እንዳትሸጥ ከዓለም ገበያ ማገድ የሚለው አንዱ ሲሆን የአውሮፓ ህብረት የነዳጅ ፍላጎቱን 40 በመቶ ከሩሲያ ሲገዛ ነበር፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ከ2027 ጀምሮ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ የሩሲያን ነዳጅ ላለመግዛት እቅድ አስቀምጦ የነበረ ሲሆን ህብረቱ ይህንን እቅዱን ማራዘሙን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ይሁንና ህብረቱ ከሩሲያ የሚገዛውን ነዳጅ ሙሉ ለሙሉ ለማቆም የወሰነበትን ጊዜ ለምን ያህል ጊዜ እንዳራዘመ ከመጥቀስ ተቆጥቧል፡፡
የአውሮፓ ሀገራት የሩሲያን ነዳጅ በቀጥታ መግዛት ባለመቻላቸው ምክንያት የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡
ይህን ተከትሎም አሁን ድረስ በርካታ የሕብረቱ አባል ሀገራት ከሩሲያ ነዳጅ በመግዛት ላይ ሲሆኑ ራሷ ዩክሬን ሳትቀር ለዓመታት የሩሲያን ነዳጅ በግዛቷ እንዲያልፍ ፈቅዳ ቆይታለች፡፡
ሩሲያ በአውሮፓ ሀገራት ማዕቀብ ቢጣልባትም ቻይና፣ ሕንድ፣ ሰሜን ኮሪያ እና ሌሎች የገበያ አማራጮችን በመጠቀም ላይ ትገኛለች ተብሏል፡፡
በተለይም በቱርክ እና አዛርባጂያን በኩል የሩሲያ ነዳጅ በአውሮፓ ወደቦች ላይ እየተሸጠ ይገኛልም ተብሏል፡፡
የሩሲያ ነዳጅ ከመካከለኛው እና አሜሪካ ከሚመረቱ የነዳጅ ምርቶች ጋር ሲነጻጸር በዋጋ ዝቅተኛ መሆኑ ለአውሮፓ ሀገራት ፈተና መሆኑ ተገልጿል፡፡