ሩሲያ ትራምፕን አሞካሽታ አውሮፓውያኑን በጦርነት ናፋቂነት ከሰሰች
የፑቲን የ21 አመታት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ፥ ያለፉት 500 አመታት የአለም ግጭትና ጦርነቶች መነሻ አውሮፓ ነው ብለዋል

የአውሮፓ መሪዎች ለዩክሬን አጋርነታቸውን ለማሳየት በእንግሊዝ እየመከሩ ነው
ሩሲያ የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም "መልካም ጅምር" አሳይተዋል ያለቻቸውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አወደሰች።
በዋይትሃውስ በትራምፕ ፊት ለተዞረባቸው የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ሞቅ ያለ አቀባበል ያደረጉትና ድጋፋቸውን ለማጠናከር ቃል የገቡትን ብሪታንያን ጨምሮ የአውሮፓ ሀገራት ደግሞ "ጦርነት ናፋቂዎች" ስትል ወቅሳለች።
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ፥ አሜሪካ እና ሩሲያ እንደ አሜሪካ-ቻይና አይነት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተና ልዩነቶች ወደ ጦርነት የማያመሩበት ግንኙነት መመስረት አለባቸው ብለዋል።
"ዶናልድ ትራምፕ ተራማጅ ሃሳብ ያላቸው መሪ ናቸው" ያሉት ላቭሮቭ፥ "አሜሪካን ዳግም ታላቅ እናደርጋታለን" የሚለው መፈክራቸውም "ሰዋዊ" ነው ማለታቸውን የሩሲያው ወታደራዊ ጋዜጣ ክራስናያ ዝቬዝዳ ዘግቧል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በየካቲት ወር መጀመሪያ ለሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ደውለው "ሰላም የሚያሰፍን መሪ" መባል እንደሚፈልጉ ነግረዋቸዋል።
የዩክሬኑ ጦርነት ሶስተኛውን የአለም ጦርነት ሊቀሰቅስ እንደሚችል በመጥቀስም የባይደን አስተዳደር በጦርነቱ ዙሪያ ይዞት የቆየውን አቋም ማብጠልጠላቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
ትራምፕ በነጩ ቤተመንግስት ዜለንስኪ ጋብዘው ያነሷቸው ነጥቦች ዩክሬናውያን እና የኬቭን የአውሮፓ አጋሮች ማስቆጣቱ አይዘነጋም።
ለዜለንስኪ ሞቅ ያለ አቀባበል ያደረጉት የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታመር የአውሮፓ ሀገራት መሪዎችን አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተው እየመከሩ እንደሚገኙ ቢቢሲ ዘግቧል።
በፑቲን አስተዳደር ለ21 አመታት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ዲፕሎማት ሰርጌ ላቭሮቭ ይህን የአውሮፓ ሀገራት ስብሰባ የዩክሬኑን ጦርነት ለማራዘመ ከመፈለግ የመነጨ መሆኑን ተናግረዋል።
"ከባይደን በኋላ ስልጣን የያዘው (የትራምፕ አስተዳደር) ጦርነቱ እንዲቆም በቀጥታ እየተናገሩ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፤ ጦርነቱን ማስቀጠል የፈለጉት እነማን ናቸው? አውሮፓውያን ናቸው" ሲሉም አብራርተዋል።
ባለፉት 500 አመታት ከቅኝ ግዛት አንስቶ በመላው አለም የታዩ ጦርነቶች ጠንሳሾች አውሮፓውያን ናቸው፤ ለዚህም ናፖሊዮን ቦናፓርቴ እና አዶልፍ ሂትለርን ማውሳት በቂ ነው ብለዋል።
ላቭሮቭ የአውሮፓ ሀገራት ወደ ዩክሬን ሰላም አስከባሪዎችን ለመላክ የያዙትን እቅድም ሞስኮ አጥብቃ እንደምትቃወመው ገልጸዋል።