የዲ.ኤች.ኤል ሰራተኞች በመመሰል 10 ሆነው ወደ አየር መንገዱ የገቡት ዘራፊዎቹ 15 ሚሊዬን ዶላር ዘርፈዋል
የታጠቁ ዘራፊዎች በቺሊ አየር መንገድ 15 ሚሊዬን ዶላር ዘረፉ
በወጉ የታጠቁና የተደራጁ ናቸው የተባሉ ዘራፊዎች ቺሊ ሳንቲያጎ ከሚገኘው አርቱሮ ሜሪኖ ቤኒቴዝ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ 15 ሚሊዬን ዶላር ገንዘብን በጠራራ ጸሃይ ዘርፈዋል፡፡
የዓለም አቀፉ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዲ.ኤች.ኤል ሰራተኞች በመመሰል 10 ሆነው ወደ አየር መንገዱ የገቡት ዘራፊዎቹ ብሪንክስ ተባለ የጸጥታ ተቋም ንብረት የሆነ መለስተኛ ተሸከርካሪን ዒላማ ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡
የዲ.ኤች.ኤል መለያ በሆኑ ቢጫና ቀይ ቀለሞች ያሸበረቀች ተሸከርካሪን ይዘው የገቡት ዘራፊዎቹ የተጠራጠሩ የአየር መንገዱን ጠባቂዎች ማስፈራራታቸውና ሊያስቆማቸው በሞከረ አንድ የጥበቃ ጓድ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውንም ሲ.ኤን.ኤን ዘግቧል፡፡
ሆርሄ ሳንቼዝ የተባሉ የሃገሪቱ ፖሊስ የምርመራ ባልደረባ ትናንት ጉዳዩን በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫን ሰጥተዋል፡፡ ሆርሄ በመግለጫቸው ልምድ ያላቸው ናቸው ያሏቸው ዘራፊዎች 14 ሚሊዬን ዶላር እና አንድ ሚሊዬን ዩሮ መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡
ተልዕኳቸውን ለመፈጸም የሚያስችል መረጃን ከውስጥ (ከአየር መንገዱ) ሳያገኙ እንዳልቀሩ ፖሊስ መጠርጠሩንም ገልጸዋል፡፡
ፖሊስ ከጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ጋር በመሆን ጉዳዩን እየመረመረ ነው ያሉት ሆርሄ በወቅቱ የነበረው የጥበቃ ሁኔታ ልል እንደነበርም ነው የተናገሩት፡፡
አየርመንገዱ ከ10 ዓመታት በፊትም ተመሳሳይ እጣ ፋንታ ገጥሞታል፡፡ 10 ሚሊዬን ዶላርም ተዘርፏል፡፡
ቺሊ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በህዝባዊ ተቃውሞዎች በመናጥ ላይ ትገኛለች፡፡