በጊኒ ዛሬ ሊደረግ የነበረው ህዝበ ውሳኔ ተራዘመ
በጊኒ ዛሬ ሊደረግ የነበረው ህዝበ ውሳኔ ተራዘመ
ጊኒያውያን በዛሬው እለት ድምጽ ይሰጡበታል ተብሎ የነበረው ማሻሻያ የተደረገበት ረቂቅ ህገመንግስት፣ የድምጽ መስጫ ጊዙ ተራዘመ፡፡
ህዝባዊ ድጋፍ ካገኘ የ81 ዓመት እድሜ ባለጸጋውን ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴን ለሶስተኛ ጊዜ እንዲወዳደሩ ይፈቅዳል የተባለው የህገ መንግስት ማሻሻያ፣ ከፍተኛ ተቃውሞን አስተናግዷል፡፡
ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ ማሻሻያውን በመቃወም በተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች በትንሹ 30 ሰዎች ተገድለዋል፡፡
በአለማቀፉ ማህበረሰብ ዘንድም የህገ መንግስት ማሻሻያው ጉዳይ ጥያቄ አስነስቷል፡፡ የአፍሪካ ህብረት እና የምእራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ኢኮዋስ (Ecowas) ድርጊቱን በመቃወም በማእድን ለበለጸገችው ሀገር የምርጫ ታዛቢዎችን እንደማይልኩ ይፋ አድርገው ነበር፡፡
ዛሬ የካቲት 22 ቀን 2012 ዓ.ም በሀገሪቱ የፓርላማ አባላትንም ለመምረጥ 7.7 ሚሊዮን ያክል ድምጽ ሰጪዎች ተመዝግበው እንደነበር የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡
በህገ መንግስቱ ላይ ይሰጣል የተባለው ድምጽ በሁለት ሳምንታት ውስጥ እንደሚካሄድ ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ ለኢኮዋስ በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡
ማሻሻያውን በጽኑ ያወገዙት የሀገሪቱ መንግስት ተቃዋሚዎች ጥምረት ህዝባዊ ተቃውሞ መጥራታቸውን ቀጥለዋል፡፡
አዲሱ የህገመንግስት ማሻሻያ የአንድ ፕሬዝዳንትን የስልጣን ጊዜ እንደቀድሞው ሁሉ ከሁለት የስልጣን ጊዜያት ባያስበልጥም አንድ የስልጣን ጊዜ ከአምስት ዓመት ወደ ስድስት ዓመት ከፍ እንዲል ይፈቅዳል ነው የተባለው፡፡
ከዚህ በላይ አሳሳቢው ጉዳይ በአዲሱ ህገመንግስት መሰረት ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ እስካሁን በመሪነት የቆዩበት ጊዜ የማይቆጠር መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም በቀጣዩ ታህሳስ ወር ሁለተኛውን የስልጣን ጊዜያቸውን የሚያጠናቅቁት ፕሬዝዳንቱ፣ በአዲስ መልክ ከዜሮ በመጀመር ለውድድር የሚቀርቡ ይሆናል፡፡