ዩኤኢ አሉባልታዎችን ወደጎን በመተው ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየሰራሁ ነው አለች
ዩኤኢ አሉባልታዎችን ወደጎን በመተው ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየሰራሁ ነው አለች
የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የሚነዙ አሉባልታዎችን ወደጎን በመተው የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እና ቫይረሱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ጉዳቱን ለመቀነስ የሰብዓዊ ተግባሯን አጠናክራ መቀጠሏን አስታውቃለች፡፡
ሀገሪቱ የምታከናውነው የጸረ ኮሮና ቫይረስ ዘመቻም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአቡ ዳቢ ልዑል እና የሀገሪቱ ጦር ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አል ነህያን መሪነት በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ልዑሉ ከዓለማቀፉ ማህበረሰብ ጋር ቫይረሱን በትብብር መቆጣጠር በሚቻልበት ጉዳይ ላይም መረጃዎችን በመለዋወጥ ላይ ይገኛሉ ነው የተባለው፡፡
ከአሜሪካው ቢሊየነር ቢል ጌትስ ጋር በዓለም የሚገኙ የተለያዩ በሽታዎችን በተለይም ኮሮና ቫይረስን ለመቆጣጠር በዓለማቀፍ እና የግለሰብ ድርጅቶች መካከል የሚደረጉ ትብብሮችን ማጠናከር እንደሚገባ መወያየታቸውን በትዊተር አድራሻቸው ገልጸዋል፡፡
ሀገሪቱ ቫይረሱን ለመከላከል የምታደርገውን ዓለማቀፍ ጥረት አጠናክራ በቀጠለችበት በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ የቱርክ ሚዲያዎች “ልዑሉ በቫይረሱ ተይዘዋል” በሚል ሆነ ብለው የሀሰት መረጃ በማሰራጨት ላይ መሆናቸውን ሀገሪቱ አስታውቃለች፡፡
አል-ዐይን ዜና በዓረብኛ ይዞት በወጣው ዘገባ እንዳስታወቀው፣ 6 የቱርክ ድረ-ገጾች የሀሰት መረጃውን በማስተጋባት ላይ ናቸው፡፡ ይሄም ሆን ተብሎ ለፖለቲካ ፍጆታ የሚደረግ ፍጹም ሀሰት የሆነ መረጃ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች 27 የቫይረሱ ተጠቂዎች ይገኛሉ፡፡ በሀገሪቱ የሚገኘው “ሰብዓዊ ከተማ” ከቻይና ሁቤይ ግዛት የሚመለሱ ዓረቦችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከ200 በላይ ዓረቦች በአቡ ዳቢ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ክትትል እየጠደረገላቸው ይገኛል፡፡
እስካሁን በመላው ዓለም የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከ100 ሺ በላይ ሲደርስ ከ3,300 በላይ ሰዎች ደግሞ ሞተዋል፡፡ ከተጠቂዎቹ አብዛኛው ቻይናውያን ሲሆኑ፣ ከቻይና ውጭ ቫይረሱ ከተዳረሰባቸው ከ80 በላይ ሀገራት ደቡብ ኮሪያ፣ ኢራን፣ ጣሊያን እና ጃፓን ዋነኞቹ ናቸው፡፡