የሄይቲ ወንበዴዎች የሀገሪቱን ዋነኛ አውሮፕላን ማረፊያ ለመቆጣጠር ተኩስ ከፈቱ
ከ4 ሺህ በላይ እስረኞችን ያስመለጡት የታጠቁ ወንበዴዎች የኬንያን ድጋፍ የጠየቁት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣን እንዲለቁ ጫናቸውን አበርትተዋል
የካሪቢያኗ ሀገር የሶስት ቀናት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብታውጅም ውጥረቱ እየተባባሰ ነው ተብሏል
የሄይቲ ወንበዴዎች በመዲናዋ ፖርት ኦው ፕሪንስ የሚገኘውን አውሮፕላን ማረፊያ ለመቆጣጠር ተኩስ መክፈታቸው ተሰማ።
ወንበዴዎቹ ከፖሊሶች እና ወታደሮች ጋር ውጊያ መጀመራቸውን ተከትሎ የቱሳይንት ሉቨርቱር አውሮፕላን ማረፊያ መዘጋቱንም አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ከሁለት የሄይቲ ዋና ዋና ማረሚያ ቤቶች ከ4 ሺህ በላይ እስረኞችን ያስመለጡት የታጠቁ ቡድኖች አውሮፕላን ማረፊያውን ሙሉ በሙሉ በእጃቸው ስለማስገባታቸው ግን እስካሁን አልተረጋገጠም።
የመዲናዋን ፖርት ኦው ፕሪንስ 80 በመቶ ይዞታ መቆጣጠራቸው የተነገረላቸው ወንበዴዎች አውሮፕላን ማረፊያውንም ሆነ ሌሎች ወሳኝ መሰረተ ልማቶችን መያዛቸው እንደማይቀር ተገምቷል።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አሪየል ሄንሪ በቅርቡ ወደ ኬንያ በማቅናት ከፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር ያደረጉት ምክክርም የወንበዴዎቹን እርምጃ እንዲጠናከር ማድረጉ ነው የተነገረው።
የአሁኑ የወንበዴዎቹ ጥቃት መባባስም የናይሮቢን ድጋፍ የሚቃወምና ጠቅላይ ሚኒስትር አሪየል ሄንሪ ስልጣን እንዲለቁ ጫና ለመፍጠር ያለመ ስለመሆኑ ተገልጿል።
“ባርቢኪው” የተሰኘው የወንበዴዎች ቡድን መሪ ጂሚ ቸርዤር፥ የሄይቲ ፖሊስ አዛዦች እና ሚኒስትሮችን በቁጥጥር ስር ማዋልና ጠቅላይ ሚኒስትር ሄነሪን ከስልጣን የማንሳት እቅድ እንዳላቸው ተናግሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቡድኑ ጥያቄ እንደማይቀበሉት ቢገልጹም አሁን ባለው የጸጥታ ሁኔታ "ወደ ቢሮዎ ለመጓዝ ስጋት የለዎትም ወይ" ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል ተብሏል።
የካሪቢያኗ ሀገር የታጠቁትን ወንበዴዎች አሳሳቢ አካሄድ ለመቆጣጠር የሶስት ቀናት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብታውጅም የጸጥታ ሁኔታዋ ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰ መሄዱን ፍራንስ 24 አስነብቧል።
የመንግስታቱ ድርጅትም በሄይቲ ወሮበላ ቡድኖች እየተፈጸመ ባለው ጥቃት የመዲናዋ ፖርት ኦው ፕሪንስ ጸጥታ አደጋ ውስጥ ገብቷል ብሏል።
የድርጅቱ ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሬክ ኬንያ የምትመራውና በርካታ ሀገራት የሚሳተፉበት የተመድ ተልዕኮ በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገባ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በሰሜን አሜሪካ አህጉር ድሃዋ ሀገር ሄይቲ በ2021 ፕሬዝዳንቷ ጆቭኔል ሞይሲ ከተገደሉ በኋላ በወሮበላ ቡድኖች ጥቃት በመታመስ ላይ ትገኛለች።