የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሀገራት ሀይቲን እንዲታደጉ ጥሪ አቅርቧል
ኬንያ አንድ ሺህ ፖሊሶችን ወደ ሀይቲ ለመላክ ተስማማች።
በዓለም ካሉ ሀገራት በድህነቷ የምትታወቀው ሀይቲ በካሪቢያን ካሉ ሀገራት መካከል ከፍተኛ አለመረጋጋት ያለባት ሀገር ናት።
አደገኛ እጽ አዘዋዋሪዎች፣ ወንበዴዎች እና አጋቾች ያሉባት ሀይቲ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳይቀር በወንበዴዎች ከሁለት ዓመት በፊት ተገድለዋል።
አሁን ላይ የሀገሪቱ 80 በመቶ በወንበዴዎች ቁጥጥር ስር የወደቀ ሲሆን አስገድዶ ደፈራ፣ እገታ እና ዝርፊያ በግልጽ የሚፈጸምባት ሀገር እንደሆነች ተመድ ገልጿል።
ተመድ በቅርቡ የዓለም ሀገራት ሀይቲን እንዲታደጉ ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ በርካታ ሀገራት ድጋፍ ለማድረግ ቃል በመግባት ላይ ናቸው።
ከነዚህ ሀገራት መካከል ጎረቤት ሀገር ኬንያ አንድ ሺህ ፖሊሶችን ወደ ሀይቲ ለመላክ መስማማቷን አስታውቃለች።
ኬንያ ፖሊሶችን ከመላክ ባለፈ በሀይቲ የሚደረገውን ህግ የማስከበር ዘመቻን የመምራት ፍላጎት እንዳላትም በውጭ ጉዳይ ሚንስቴሯ ቡኩል አስታውቃለች።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር በስልክ ማውራታቸውን እና የኬንያውን ውሳኔ ማድነቃቸው ተገልጿል።
ጉቴሬዝ አክለውም ተመድ ለኬንያ አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚሰጡ ቃል መግባታቸውም ተገልጿል። ከቀናት በፊት ዜጎቿ ሀይቲን ለቀው እንዲወጡ ጥሪ ያቀረበችው አሜሪካም የኬንያን ውሳኔ አድንቀዋል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከንም ከፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር በስልክ ማውራተቸውን እና ዋሽንግተን ሁሉንም አይነት ድጋፍ ለኬንያ እንደምታደርግ ተናግረዋል ተብሏል።
የጸጥታው ምክር ቤት በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ሀይቲ ለገጠማት ቀውስ መፍትሄ ምክረ ሀሳብ እንዲቀርብለት ከሰሞኑ አዲስ ውሳኔ ማስተላለፉ አይዘነጋም።