ኬንያ በሀይቲ ወንበዴዎችን ለመፋለም ፈቃድ አገኘች
የሀገሪቱ ፕሬዝዳን ከተገደሉ ወዲህ ወንበዴዎች የሀገሪቱን ሰፊ ክፍል ተቆጣጥረው እያሸበሩ ነው ተብሏል
ሀይቲ የተመድን ውሳኔ ለረጅም ጊዜ ለተሰቃዩ ዜጎቿ የተስፋ ብርሃን ነው ብላለች
የሀይቲ ጠቅላይ ሚንስትር ያቀረቡትን የድረሱልኝ ጥያቄ የተቀበለው የመንግስታቱ ድርጅት ኬንያ የደህንነት ስራ እንድትራ ድጋፍ ሰጥቷል።
የካረቢያኗ ሀገር ለአስርት ዓመታት በወንበዴዎች ግጭት ስትታመስ ቆይታለች። ሆኖም ፕሬዝዳንት ጆቨኔል ሞሲ በፈሰንጆቹ 2021 ከተገደሉ ወዲህ በሀገሪቱ ግፍ መስፋፋቱ ተነግሯል።
ወንበዴዎች የሀገሪቱን ሰፊ ክፍል መቆጣጠራቸው የተነገረ ሲሆን፤ በመቶዎች የሚቆጠሩትን በመግደል በነዋሪዎች ላይ ሽብር ከፍተዋል ተብሏል።
የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ወንበዴዎችን ለመደምሰስና ስርዓትን ለመመለስ "ጠንካራ እርምጃ" መውሰድ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የተመድ የጸጥታው ም/ቤት ባሳለፈው ውሳኔ አንድ ዓመት የሚቆይ ተልዕኮ ያጸደቀው ሲሆን፤ በዘጠኝ ወራት ግምገማ እንደሚያካሂድም ገልጿል።
በውሳኔው መሰረት አዲሱ ኃይል የሁለትዮሽ የጸጥታ ተልዕኮዎችን እንደሚያካሂድና ከሀይቲ ፖሊስ ጋር በመተባበር እስር የመፈጸም ስልጣን አለው።
ከ2016 ወዲህ ምርጫ ላላደረገችው ሀገር ምርጫን እንድታሰናዳ አስቻይ ሁኔታ መፍጠር ሌላኛው ግቡ መሆኑ ተነግሯል።
ሀይቲ ውሳኔውን ለረጅም ጊዜ ለተሰቃዩ ዜጎቿ የተስፋ ፍንጣቂ ነው ብላዋለች።
ኬንያ አንድ ሽህ የፖሊስ መኮንኖችን ወደ ሀይቲ እንደምትልክ የተናገረች ሲሆን፤ ተልዕኮው በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት መጀመሪያ ላይ እንደሚጀመር ተናግራለች።