በናይጄሪያ በርካታ ሴት ተማሪዎች በታጣቂዎች ታፍነው ተወሰዱ
በሀገሪቱ እየተለመደ የመጣው የተማሪዎች ዕገታ በመማር ማስተማር ስርዓቱ ላይ ተጽዕኖው እየጎላ መጥቷል
የዛሬው ከታህሳስ ወር ወዲህ በአፍሪካ ቁጥር አንድ የህዝብ ቁጥር ባላት ሀገር በገፍ የተፈጸመ ሦስተኛው ዕገታ ነው
በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ ዛሬ አርብ ማለዳ ላይ ታጣቂዎች በዛምፋራ ግዛት የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤትን በመውረር በርከት ያሉ ተማሪዎችን አፍነው ወስደዋል፡፡ ይህም እ.ኤ.አ. ከታህሳስ ወር ወዲህ በአፍሪካ ቁጥር አንድ የህዝብ ቁጥር ባላት ሀገር በገፍ የተፈጸመ ሦስተኛው ጠለፋ ነው፡፡
የዛሬውን የተማሪዎች መታገት የገለጹት የዛምፋራ ግዛት ቃል አቀባይ የታገቱ ተማሪዎቹ ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ አልገለጹም፡፡
ለአፈናው ኃላፊነቱን የወሰደ አካል ባይኖርም “ሽፍቶች” በመባል የሚታወቁት የወንጀል ቡድኖች በአካባቢው በአፈና ይታወቃሉ፡፡
“ሽፍቶቹ እንደተለመደው የመንደሩን ነዋሪዎች ሊያጠቁ የመጡ መስሎን ነበር ፤ ነገር ግን በስተመጨረሻ ተማሪዎችን አግተው ሔደዋል” ሲሉ ቤሎ ማይኩሳ የተባሉ የ52 ዓመት ጎልማሳ ተናግረዋል፡፡ ታጥቀው የመጡት ጠላፊዎቹ ከፍተኛ ተኩስ ከፍተው የነበረ ሲሆን ዓላማቸውም ሰዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ሊሆን እንደሚችልም ግለሰቡ ገምተዋል፡፡
የአሁኑ እገታ የተፈጸመው በሰሜን ማዕከላዊ ናይጄሪያ በተመሳሳይ በትምህርት ቤት በተፈጸመ ጥቃት 27 ተማሪዎችን ጨምሮ 40 ሰዎች ታግተው ከተወሰዱ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው፡፡
ባለፈው ታህሳስ ወር ደግሞ በሰሜንምዕራብ ናይጄሪያ ካጺና ግዛት ከሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት 300 ወንድ ተማሪዎች የታገቱ ሲሆን ለዚህም ቦኮ ሀራም ኃላፊነቱን ወስዷል፡፡ ይሔው ጽንፈኛ ታጣቂ ቡድን እ.ኤ.አ. በ2014 270 የቺቦክ ሴት ተማሪዎችን በማገት መነጋገሪያ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ያኔ ከታገቱት ተማሪዎች 100 የሚሆኑት እስካሁን ያሉበት አይታወቅም፡፡
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ እለት የናይጄሪያ ጦር በሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላትን ከተማ ከአሸባሪዎች መልሶ መቆጣጠሩን መግለጹ ይታወሳል፡፡ ጦሩ በአየር ኃይል ጭምር በመታገዝ በአሸባሪ እና ጽንፈኛ ቡድኖች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን በተደጋጋሚ ቢያሳውቅም ፣ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተማሪዎች ላይ የሚፈጸሙ እገታዎች ስጋት ከመፍጠራቸው ባለፈ በትምህርት ስርዓቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በማሳደር ላይ ናቸው፡፡