አርመን ለእስራኤል-ፍልስጤም ግጭት የመጨመሻ መፍትሄ የሚሆነው 'ቱ ስቴት ሶሉሽን' ነው ብላለች
አርመን ለፍልስጤም የነጻ ሀገርነት እውቅና ሰጠች።
አርመን ለፍልስጤም የነጻ ሀገርነት እውቅና መስጠቷን የሩሲያው ታስ የዜና አገልግሎት የአርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠቅሶ ዘግቧል።
በዚህ የተቆጣችው እስራኤል፣ በእስራኤል የሚገኙትን የአርመን አምባሳደር ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ጠርታለች።
የአርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቫሀን ኮስታኒያን "ለፍልስጤም እና እስራኤል ግጭት መፍትሄ 'ቱ ስቴት ሶሉሽንን' ወይም ከእስራኤል ጎን የፍልሰጤም ሀገር መቋቋምን የምትደግፈው አርመኒያ፣ ለፍልስጤም የነጻ ሀገርነት እውቅና ለመስጠት ከውሳኔ ደርሳለች" ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በጽረ ገጹ ባሰፈረው ረጅም ጽሁፍ "በጋዛ ያለው አስከፊ ሰብአዊ ቀውስ እና እየተካሄደ ያለው ወታደራዊ ግጭት መፍትሄ ከሚፈልጉት አለምአቀፍ የፖለቲካ አጀንዳዎች አንዱ ነው" ሲል ገልጿል።
በጋዛ በንጹሃን እና በመሰረተልማት ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ያወገዘው ሚኒስቴሩ በሃማስ እጅ ያሉ 120 ታጋቾችም እንዲለቀቁ ጥሪ አቅርቧል።
"የአርመን ሪፐብሊክ የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ያቀረበውን ምክረ ሀሳብ ትደግፋለች" ብሏል መግለጫው።
የአርመን መንግስት በመካከለኛው ምስራቅ ስላም እንዲሰፍን እና በአይሁዶች እና በፍልስጤማውያን መካከል የመጨረሻ እርቅ እንዲፈጠር ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ሚኒስቴሩ ጠቅሷል።
የእስራኤል-ፍልስጤም ግጭት የመጨመሻ መፍትሄ የሚሆነው 'ቱ ስቴት ሶሉሽን' ነው ብሎ እንደሚያምን ሚኒስቴሩ አክሎ ገልጿል።
ከፈረንጆቹ 1988 ጀምሮ 145 ሀገራት ለፍልስጤም የሀገርነት እውቅና የሰጡ ሲሆን ባርባዶስ፣ጃማይካ፣ትሪንዳድ እና ቶቤጎ፣ ባህማስ፣ ኖርዌይ፣ ስፔን፣ አየርላንድ፣ስሎቨኒያ በቅርቡ እውቅና መስጠታቸው የሚታወስ ነው።
የእስራኤል-ፍልስጤም ጦርነት ወደ ተኩስ አቁም እንዲያመራ ጫና ቢደረግም፣ ሁለቱ አካላት በቅደመ ሁኔታዎች ላይ ባለመስማማታቸው እስካሁን እውን አልሆነም።