የሊባኖስ ፓርላማ የጦር መሪውን ጀነራል ጆሴፍ አውንን ፕሬዝዳንት አድርጎ መረጠ
አዲሱ ፕሬዝዳንት ከአሜሪካ እና ሳኡዲ አረብያ ድጋፍ እንዳላቸው ተነግሯል
ለሁለት አመታት ያለ መሪ የሰነበተችው ሀገር ፕሬዝዳንት ከሄዝቦላህ፣ ከኢራንና ከሌሎችም ተጽዕኖ ሊያጋጥማቸው ይችላል ተብሏል
የሊባኖስ ፓርላማ ለዓመታት የዘለቀው የፖለቲካ አለመግባባት እና የፕሬዚዳንት ክፍተት ይሞላሉ የተባሉትን የጦር አዛዥ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አድርጎ መርጧል።
በአሜሪካ እና ሳኡዲ አረብያ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳላቸው የሚነገርላቸው የሀገሪቱ ጦር አዛዥ ጀነራል ጆሴፍ አውን ከሁለት ዙር ድምጽ በኋላ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል።
ከጀኔራል ጆሴፍ አዎን በተጨማሪ ፤ በአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት እና የቀድሞ የገንዘብ ሚኒስትር ጂሃድ አዙር እንዲሁም የሀገሪቱ ደህንነት ኤጂንሲ ሀላፊ ሜጀር ጄኔራል ኤልያስ አልባይሳሪ ለፕሬዝዳንት እጩ ሆነው ቀርበው ነበር፡፡
በኢራን እና በሄዝቦላህ የሚደገፉት የቀድሞ የሊባኖስ ፕሬዝዳንት ሚሼል አውን የስልጣን ዘመን ካበቃበት ጥቅምት 2022 ጀምሮ ቤሩት ለሁለት አመታት ፕሬዝዳንት አልባ ሆና ቆይታለች፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከስልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ ምዕራባውያንን በሚደግፉ እና ኢራንን በሚደግፉ የሀገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በተፈጠረ ልዩነት ነው ሀገሪቱ መሪ መሰየም ተስኗት የቆየችው፡፡
ከዛሬው የፓርላማ ድምጽ አሰጣጥ በፊት ሊባኖስ ፕሬዝዳንት ለመምረጥ 12 ያልተሳኩ ሙከራዎችን አድርጋለች፡፡
ባለፈው ህዳር በአሜሪካ አደራዳሪነት በሄዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ሲጠበቅ የነበረውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዲፋጠን እንዳደረገው ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ሄዝቦላህ በእስራኤል በደረሰበት ጥቃት የአመራር እና ወታደራዊ አቅሙን ማጣት ፣ የሀማስ መዳከም እንዲሁም የበሽር አላሳድ መንግስት ውድቀት በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠናዊ የቅርጽ ለውጥን ያስከተሉ ሁነቶች ስለመሆናቸው ይነገራል፡፡
የሊባኖስ ጦር ከእስራኤል ጋር በተደረገው ሁለንተናዊ ጦርነት ውስጥ አልተሳተፈም ነገር ግን የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ቁልፍ ተዋናይ ነው።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ የሀገሪቱ ብሔራዊ ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ በሄዝቦላህ ቁጥጥር ስር ባሉ እና ከእስራኤል ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች ማሰማራት እንዳለበት ይደነግጋል፤ የእስራኤል ጦር ከሊባኖስ ግዛት እንዲወጣም ይጠይቃል።
በፖለቲካ ፣ በጦርነት እና በማህበራዊ ቀውስ ውስጥ የምትገኝውን ሀገር ከአመታት በኋላ በቋሚ መሪነት የተሾሙት ፕሬዝዳንት ሀገሪቱን ማረጋጋት ላይ ትልቅ የቤት ስራ የሚጠብቃቸው ይሆናል፡፡
የማሮናይት ክርስትና እምነት ተከታይ እንደሆኑ የተነገረላቸው ጀነራል ጆሴፍ የሄዝቦላህ ፣ የኢራን እና የሌሎች ቀጠናዊ ተዋናዮችን ጫና ተቋቁመው የተረጋጋ መንግስት መመስረት ፈተና ሊሆንባቸው እንደሚችልም ተነግሯል።