የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር የሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነትን "በመርህ ደረጃ" መቀበላቸው ተገለጸ
የሰላም ስምምነት ሀሳቡ ለ60 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም በማስተግበር በዘላቂነት ጦርነት ማስቆምን አላማው አድርጓል
የአሜሪካ ልዩ ልዑክ በስምምነቱ የመጨረሻ ሂደቶች ዙሪያ ለመምከር በመጪው ረቡዕ ወደ ቤይሩት ያቀናል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከሄዝቦላህ ጋር የተጀመረውን የተኩስ አቁም ስምምነት ሀሳብ "በመርህ ደረጃ" መቀበላቸው ተሰማ፡፡
እሁድ ምሽት ከእስራኤል ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት የፀጥታ ምክክር ሀሳቡን በ "በመርህ ደረጃ" ማፅደቃቸውን ሲኤንኤን ጉዳዩን ያውቃሉ ያላቸውን ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
በዛሬው እለት ለሊባኖስ መንግስት ይተላለፋል ተብሎ በሚጠበቀው የስምምነት ሰነድ ላይ እስራኤል ያላትን የሀሳብ ልዩነቶች እንደምታንጸባርቅ ነው የተነገረው፡፡
ምንም እንኳን ቴልአቪቭ እንዲስተካከሉ የምትፈልጋቸው የሰነዱ ሀሳቦች ካልተስተካከሉ ስምምነቱን ሙሉ ለሙሉ መቀበሏን ማረጋገጫ ባይሆንም ከበርካታ ወራት በኋላ ለስምምነት የቀረበው ሰነድ ይህኛው እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የተኩስ አቁም ስምምነት ለፊርማ ከመቅረቡ በፊትም በሀገሪቱ የካቢኔ ምክር ቤት መጽደቅ ይኖርበታል፡፡
ድርድሩን የሚያውቁ ምንጮች እንዳሉት “ንግግሮች በአወንታዊ መልኩ ወደ ስምምነት እየተጠጉ ነው፤ ነገር ግን በእስራኤል እና ሄዝቦላህ መካከል የቀጠለው የተኩስ ልውውጥ አንድ የተሳሳተ እርምጃን ቢያስከትል ውይይቱን ሊያሰናክል ይችላል።”
በቀጠናው የአሜሪካ ልዩ ልዑክ አሞስ ሆይስተን ባለፈው ሳምንት በቤይሩት ባደረጉት ንግግር “በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ለፍጻሜ ቀርቧል፤ ነገር ግን ለስኬታማነቱ የሁለቱን ተደራዳሪዎች በጎ ፈቃድ ይፈልጋል” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የሊባኖሱ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ እና የፓርላማ አፈጉባዔው ናቢህ በሪ ከሄዝቦላህ መሪዎች ጋር ተገናኝተው ገንቢ እና ክፍተቶቹን ማጥበብ የሚያስችል ውይይት አካሄድዋል ነው ያሉት፡፡
ልዩ ልኡኩ አሞስ ሆይስተን በድርድሩ የመጨረሻ ሂደቶች ዙርያ ለመምከር በመጪው ረቡዕ ወደ ሊባኖስ እንደሚያቀኑም ተዘግቧል፡፡
በአሜሪካ የሚደገፈው የሰላም ስምምነት ሀሳብ ለ60 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም በማስተግበር ዘላቂ የሆነ ጦርነት ማስቆምን ተፈጻሚ ማደረግ አላማው አድርጓል፡፡