እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንድታከብር ምዕራባውያን ተጽእኖ እንዲያደርጉ ሊባኖስ ጠየቀች
በትላንትናው ዕለት በተለያዩ የሊባኖስ ከተሞች እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት 11 ሰዎች ተገድለዋል
ሄዝቦላህ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል በመተኮስ ለጥቃቱ የአጸፋ ምላሽ ሰጥቷል
የሊባኖስ ከፍተኛ ባለስልጣናት አሜሪካ እና ፈረንሳይ እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱን መጣስ እንድታቆም ግፊት እንዲያደርጉ ጠየቁ፡፡
እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ ላይ ከፍተኛ ጥቃት መፈጸሟ እና ሄዝቦላህ በእስራኤል ወታደራዊ ካምፕ ላይ ሰኞ ዕለት ሮኬት ማስወንጨፉን ተከትሎ ተግባራዊ መደረግ ከተጀመረ ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የተጣሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ዘላቂነት ላይ ጥያቄ ፈጥሯል፡፡
የሊባኖሱ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ እና የፓርላማ አፈጉባዔ ናቢህ በሪ ከዋይት ኃውስ እና ከፈረንሳይ ፕሬዝደንት ቢሮ ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት የተኩስ አቁሙ በአደገኛ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
ታሉሳ እና ሃሪስ በተባሉ የደቡባዊ ሊባኖስ አካባቢዎች ትላንት በተፈጸመ ጥቃት 9 ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ ሶስት ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡
እስራኤል በጥቃቱ በደረዘን የሚቆጠሩ የሄዝቦላህ ኢላማዎች ላይ ጥቃት ማድረሷን አምናለች፡፡
በትላንትናው እለት በሌሎች የሊባኖስ አካባቢዎች በተፈጸመ ጥቃት አንድ የመንግስት የጸጥታ አባልን ጨምሮ ሁለት ሰዎች ሲገደሉ በአጠቃላይ በትላንቱ ጥቃት የሞቱ ሰዎችን ቁጥር 11 አድርሶታል፡፡
በአሜሪካ የሚመራ የተኩስ አቁም ስምምነት ሂደቱን የሚከታተል እና የስምምነት ማስፈጸሚያዎችን የማገዝ ሃላፊነት የተሰጠው ቡድን ተቋቁሟል። ነገርግን እስካሁን ሥራ አልጀመረም።
እስካሁን ቢያንስ 54 የተኩስ አቁም ጥሰቶች በእስራኤል መፈጸማቸውን የምትገልጸው ቤይሩት ሀገሪቱ ስምምነቱን እንድታከብር ጠይቃለች፡፡
እስራኤል በበኩሏ በሊባኖስ የቀጠለችዉ ወታደራዊ እንቅስቃሴ የተኩስ አቁምን ለማስፈጸም ያለመ እና በስምምነቱ ወቅት የገባቻቸውን ግዴታዎች የማይጥስ ነዉ ብላለች ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማት ሚለር ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራርያ የተኩስ አቁም ተግባራዊነቱ መቀጠሉን ገልጸው በሁለቱም ወገኖች በኩል ጥሰቶች ስለመፈጸማቸው ተናግረዋል፡፡
የሊባኖስ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚካቲ በትላንትናው ዕለት የተኩስ አቁም ሂደቱን የሚቆጣጠረው ቡድን መሪ የአሜሪካው ጄነራል ጃስፐር ጅፍሪ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በዚህ ወቅትም የእስራኤል ጦር በአፋጣኝ ከሊባኖስ ድንበር ለቆ መውጣት የስምምነቱን መጽናት የሚያረጋግጥ ወሳኝ እርምጃ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የተኩስ አቁም ስምምነት እስራኤል በሊባኖስ ወታደራዊ ዘመቻዎችን ከማድረግ እንድትቆጠብ የሚከለክል ሲሆን፤ ሄዝቦላህን ጨምሮ የታጠቁ ቡድኖች በእስራኤል ላይ ጥቃት እንዳይሰነዝሩ ማድረግን ይጠይቃል።
በተጨማሪም የእስራኤል ወታደሮች ከደቡብ ሊባኖስ ለቀው እንዲወጡ የ60 ቀናት ጊዜ ሰጥቷል።