ከሁለት ሳምንታት በፊት በቁጥጥር ስር የዋሉት የትግራይ ቴሌቭዥን ጋዜጠኞች አስካሁን ፍርድ ቤት አልቀረቡም ተባለ
ጋዜጠኞቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት “ከጠላት ጋር ተባብራችኋል” በሚል ነው እንደሆነም ነው የተገለጸው
የመቀለ ከተማ ዓቃቤ ህግ ”ጋዜጠኞቹ የታሰሩት በሙያቸው ሳይሆን በሌላ ወንጀል ነው” ብሏል
ከሁለት ሳምንታት በፊትበትግራይ ክልለ መቀል ከተማ በቁጥጥር ስር የዋሉት የትግራይ ቴሌቭዥን ጋዜጠኞች አስካሁን ፍርድ ቤት አልቀረቡም ተባለ፡፡
አል-ዐይን አማርኛ ከምንጮቹ ለማረጋገጥ እንደቻለው ከጠላት ጋር ተባብራችኋል ተብለው ለእስር የተዳረጉት የትግራይ ጋዜጠኞች ምስግና ስዩም፣ ሐበን ሃለፎም፣ ሃይለሚካኤል ገሰሰ፣ ተሾመ ጠማለው እና ዳዊት መኮንን ናቸው፡፡
ከጋዜጠኞቹ በተጨማሪ የተቋሙ የፋይናንስ ባለሙያ የነበረው ክፍሎም አጽብሃ መታሰሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የታሰሩት ጋዜጠኖች በተለይም አራቱ በቁጥጥር ስር ከዋሉ ሁለት ሳምንታት ቢሆናቸውም፤ እስኩሁን ለፍርድ አለመቅረባቸው ጥያቄ እያስነሳ ይገኛል፡፡
የሐበን ሃለፎም ጠበቃ አቶ መስፍን አርአያ ሰሞኑን ከቪኦኤ ጋር በነበራቸው ቆይታ “ ‘ጠላት’ የሚለው ክስ ግልጽ ባይሆንም ከብልጽግና ጋር ተባብራቿኋል የሚል ሊሆን ይችላል” ብለዋል፡፡
ጠበቃው በጥብቅና የያዙት ተከሳሽ እስካሁን ፍርድ ቤት አለመቅረቡ ቅሬታ እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
“ጋዜጠኞቹ የታሰሩበት ስፍራ ንጽህና የሚጎድለው ነው፤ የነሱ መታሰር ለጋዜጠኝነት ሙያ የሚጎዳ ነው” ሲሉም አክለዋል አቶ መስፍን፡፡
የመቀሌ ከተማ ዓቃቤ ህግ አዲስ ገ/ስላሴ በበኩላቻው ”ጋዜጠኞቹ የታሰሩት በሙያቸው ሳይሆን በሌላ ወንጀል ነው፤ ለዚህም አስፈላጊውን የማጣራት ሂደት እያደረግን ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት ጋዜጠኞች ምስግና ስዩም እና ተሾመ ጠማለው እሰካሁን በተቋሙ ውስጥ ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን፤ ሐበን ሃለፎም፣ ሃይለሚካኤል ገሰሰ እና ዳዊት መኮንን ደግሞ ቀደም ሲል በተቋሙ የተካሄደውን “ግምገማ” ተከትሎ ከስራ ታግደው የቆዩ መሆናቸው አል-ዐይን ከምንጮቹ አረጋግጧል፡፡
ጋዜጠኛ ሐበን ሃለፎም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ክልሉን በሚያስተዳድርበት ወቅትም ቢሆን ከሳምንት በላይ ለሚሆኑ ጊዜያት ታስሮ የነበረ ነው፡፡
የትግራይ ቴሌቭዥን ጋዜጠኞች ፤ ባለፈው ዓመት ክልሉ ሲያስተዳደሩ በነበሩ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አባለትም ሆነ በፌደራል መንግስት አካላት በሚፈለገው መልኩ እየሰሩ አይደለም ተብለው ሲወቀሱ እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡
ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግስት እያካሄድኩ ነው ባለው የህግ ማስከበር ዘመቻ ጋዜጠኞች እና የማህበረሰብ አንቂዎች ታስረዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እስሩ ተገቢ አይደለም ሲል መንግስትን ተችቷል።