ህወሓት "የትግራይ ግዛቶችን በሰላምም ሆነ በጦርነት እናስመልሳለን" ሲል ዛተ
በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚካሄደው የሰላም ጥረት እስካሁን ይህ ነው የሚልባል ውጤት አላማጣም
ህወሓት ምእራብ ትግራይ በማለት የሚጠራው አካባቢ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ስር እየተዳደረ ይገኛል
መንግስት በሽብርተኝነት የፈረጀው ህወሃት የትግራይ ግዛት የነበሩ ቦታዎች በማንኛውም አማራጭ እንደሚያስመልስ ዝቷል፡፡
የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ከሰሞኑ ድርድር ይደረጋል በተባለው ጉዳይ ላይ አስተያየት ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በህግ ከሚፈልጋቸው የህወሓት አመራሮች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ጌታቸው በፈረንሳዩ ለሞንዴ ጋዜጣ ላይ ስለድርድር በተጻፈው ጹሑፍ ላይ ነው ሃሳብ የሰጡት።
ጋዜጣው ስማቸው ያልተገለፀ ዲፕሎማቶችን ጠቅሶ የትግራይ እና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጥንቃቄ የተሞላበት ውይይት እንደሚያደርጉ ገለጾ ነበር። በተጨማሪም ህወሃት "ምዕራብ ትግራይ" እያለ የሚጠራቸውን አካባቢዎች ይገባኛል ማለቱን ትቷል ሲል ጋዜጣው ቢጽፍም አቶ ጌታቸው አልተውንም ብለዋል።
አቶ ጌታቸው በቅርቡ እነዚህን የይገባኛል ጥያቄዎች በይፋ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።
"የትግራይ መንግስት ያወጀው ዓላማና አቋም ነው፣ እያንዳንዱን ኢንች የትግራይን ግዛት በሚቻለው መንገድ ሁሉ በሰላማዊም ሆነ በሌላ አካሀድ ለማስመለስ ሁሉንም እናደርጋለን" ብለዋል።
መንግስትና ህወሃት በታንዛኒያ ሊደራደሩ ነው መባሉን ተከትሎ መንግስት የሠጠው ምላሽ የለም።
ህወሓት ምዕራብ ትግራይ በሚል የሚጠራቸው ቦታዎች አሁን ላይ በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገደ ሰቲት ዞን አካል ናቸው። ትግራይ እና አማራ ክልሎችን የሚያወዛግቡት ራያ እና ወልቃይት አሁንም የጭቅጭቅ እና የግጭት መንስኤ ሆነው ቀጥለዋል።
ከዚህ ቀደም ሲልም ራያና ወልቃይት የአማራ ክልል ግዛቶች ናቸው በሚል ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ተቋቁሟል።
ከ 2010 በፊት የነበረው የትግራይ ክልል መንግሥት ግን ጥያቄዎቹን ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብአዊ እርዳታ ሲባል ግጭት ማቆሙን ካወጀ በኋላ በፌደራል መንግስትና በህወሓት ሃይሎች መካከል ያለው ጦርነት ጋብ ያለ ቢመስልም፤ድጋሚ ጦርነት ይቀሰቀሳል የሚል ስጋትአለ፡፡በአሜሪካ ድጋፍ እና በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚካሄደው የሰላም ጥረት እስካሁን ይህ ነው የሚባል ውጤት አላማጣም፡፡