ቴድሮስ አድሃኖም ዓለም ለዩክሬን የሰጠውን ትኩረት ያህል ለትግራይ አልሰጠም ሲሉ ተናገሩ
ራሳቸው ዶ/ር ቴድሮስ ዓለም አቀፍ ተቋምን እየመሩ ገለልተኛ አይደሉም በሚል ይወቀሳሉ
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ዓለም ጥቁሮችን እንደነጮች ሁሉ እኩል እየተመለከተ እንዳይደለ ተናግረዋል
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ዓለም ለዩክሬን የሰጠውን ትኩረት ያህል ለትግራይ እንዳልሰጠ ተናገሩ፡፡
ዓለም የጥቁሮችን ችግሮች እንደነጮች ሁሉ በእኩል ዐይን ተመልክቶ እንደማያስተናግድ የተናገሩት ዶ/ር ቴድሮስ ለዩክሬን ከተሰጠው ትኩረት ሽራፊ ያህሉ ለአፍሪካ እንዳልተሰጠ ተናግረዋል፡፡
"ዓለም በእውነት ለጥቁርና ለነጭ ህይወት እኩል ትኩረት ይሰጥ እንደሁ አላውቅም" ሲሉ ትናንት በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተናገሩት ዶ/ር ቴድሮስ፡፡
ትልቅ ዓለም አቀፋዊ ጉዳይ መሆኑን ተከትሎ ሙሉ የዓለም ትኩረት ዩክሬን ላይ መሆኑ ባይከፋም ሽራፊ ያህሉ ትኩረት ለትግራይ፣ ለየመን፣ ለአፍጋኒስታን፣ ለሶሪያ እና ለሌሎች አለመሰጠቱንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡
ሁኔታው "በጣም የሚያምና ለመቀበል የሚቸግር" ቢሆንም በገሃድ እየሆነና "አንዳንዶች ከሌሎች የበለጠ እኩል" ሆነው እየታዩ ነው ያሉት ዶ/ር ቴድሮስ "ዓለም የሰው ልጆችን እኩል እየተመለከተችና እያስተናገደች እንዳልሆነ በድፍረት መናገር አለብኝ ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ እና ጤና ሚኒስትር በትግራይ ያለው ሁኔታ እጅጉን ያሳስበኛልም ነው ያሉት፡፡
ቴድሮስ አድሃኖም በኢትዮጵያ ጉዳይ የግል አቋማቸውን እንዳያንጸባርቁ ኢትዮጵያ ጠየቀች
መንግስት ሙሉ በሙሉ ተኩስ ማቆሙን ተከትሎ በቀን እርዳታ የጫኑ 100 ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ እንዲገቡ ስምምነት ላይ ቢደረስም ይህ እየሆነ አይደለም "እስካሁን 20 የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ብቻ ናቸው ወደ ክልሉ የገቡት" እንዳሉት እንደ ዶ/ር ቴድሮስ ገለጻ፡፡
ይህ "ለዲፕሎማሲው ሲባል ብቻ" በመንግስት የተደረገ ሊሆን ይችላልም ብለዋል፡፡
እስካሁን በትንሹ 2000 ገደማ የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ትግራይ ሊደርሱ ይችሉ እንደነበርም ነው ያስቀመጡት፡፡ የቀድሞው የህወሓት ስራ አስፈጻሚ አባል የመንግስትና የኤርትራ ወታደሮች ከበባ አሁንም ስለመቀጠሉ ተናግረዋል፤ ዓለም ወደ ቀልቡ ተመልሶ የሰው ልጆችን ሁሉ በእኩልነት እንደሚያይ ተስፋ ማድረጋቸውን በመጠቆም፡፡
በኢትዮጵያ ሰዎች በብሄራቸው ምክንያት ያለምንም ወንጀል በህይወት እያሉ ጭምር በእሳት እንዲቃጠሉ መሆኑም ተናግረዋል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ ራሳቸው ዓለም አቀፍ ተቋምን እየመሩ ገለልተኛ አይደሉም በሚል ይወቀሳሉ፡፡ ልክ እንደ ትግራይ ሁሉ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ስላጋጠሙ ችግሮችና ህወሓት እንደፈጸማቸው ስለሚነገሩ ወንጀሎች በአደባባይ አይናገሩም በሚልም ስማቸው ይነሳል፡፡
ፖለቲካዊ ውግንና እንዳላቸው የገለጸችው ኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት የጤና ተቋማት ሲወድሙ ምንም ለማለት አለመቻላቸውን በማስታወስ ኢትዮጵያን ከተመለከቱ የትኞቹም ጉዳዮች ራሳቸውን እንዲያርቁ መጠየቋ ይታወሳል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ስልጣናቸውን አላግባብ እየተጠቀሙበት ነው ስትል ኤርትራ መክሰሷም አይዘነጋም።