ትግራይ ክልል ያሉ ነዋሪዎች ገንዘብ እንዴት እያገኙ ነው?
የፋይናነስ ተቋማት አለመኖራቸውን ተከትሎ በርካቶች በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች በኩል ገንዘብ ለመላክ ተገደዋል
ህገ-ወጥ የገንዘብ አዘዋዋሪዎች ከሚላከው ገንዘብ ከ30 እስከ 50 በመቶ ቆርጠው እንደሚያደርሱ ይነገራል
ከአንድ ዓመት ከሰባት ወራት በፊት የተጀመረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከትግራይ በተጨማሪ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ደርሷል፤ ትምህርት እና የጤና ተቋማትን ጨምሮ በርካታ የህዝብ መገልገያ የሆኑ መሰረተ ልማቶች ወድመዋል።
ጦርነቱ ሶስቱንም ክልሎች ቀድሞ ከነበሩበት የሰላምም ሆነ የምጣኔ ሃብት ይዞታ ሌሎች እንቅስቃሴዎችም ውጭ ያደረገም ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድቷል” ባሉለት በትግራይ ክልል መድሃኒት፣ ምግብ፣ ገንዘብ፣ የቴሌኮም እና የትራንስፖርት አገልግሎት አለመኖሩ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ስራቸውን እንዲጀምሩም ተደጋጋሚ ጥያቀዎች ይቀርባሉ፡፡
ዛሬ ላይ ህይወት እጅጉን የፈተናቸው የትግራይ ክልል ነዋሪዎች የሚበላ እና የሚላስ አጥተው ያላቸውን ንብረት እስከ መሸጥ የደረሱበት፤ አለፍ ሲልም ለልመና በአደባባይ የሚታዩበት ሁኔታ መፈጠሩን አል-ዐይን አማርኛ የመቀሌ ነዋሪዎችን አነጋግሮ ማስነበቡ ይታወሳል።
አል-ዐይን አማርኛ ባገኘው መረጃ መሰረት ከትግራይ ክልል አዲስ አበባም ሆነ በውጭው ሀገራት ለሚገኙ ዘመዶቻቸው ስልክ ለመደወልና ገንዘብ እንዲልኩላቸው ለመጠየቅ ወደ አላማጣ የሚመጡ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው።
አሁን ላይ ከመሃል እና ከተለያዩ የትግራይ አቅጣጫዎች ወደ አላማጣ እየመጣ ያለው ሕዝብ ከአቅም በላይ በመሆኑ በየበረንዳው፣ በቤተ ክርስቲያናት፣ በመስጊዶች፣ በጋራዦች እና በስታዲየም ሲውል ሲያድር መመልከት የተለመደ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።
ትግራይ ክልል ያሉ ነዋሪዎች ገንዘብ እንዴት እያገኙ ነው?
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት ያሉ ዜጎች በትግራይ ክልል ለቤተሰቦቻቸው ገንዘብ ለመላክ የፋይናነስ ተቋማት ዝግ መሆናቸውን ተከትሎ በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች በኩል ገንዘብ ለመላክ መገደዳቸውን ይናገራሉ።
ነገሩን አስቸጋ የሚያደርገው፤ ከሀገር ውስጥም ሆነ ውጭ ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው የገንዘብ እንዲላክላቸው ፈልገው ወደ አላማጣ የሚመጡ ሰዎች፤ በህገ ወጥ በገንዘብ አዘዋዋሪዎች የሚንገላቱና ከሚላክላቸው የገንዘብ መጠን እስከ 50 በመቶ የሚቆረጥ መሆኑ ነው።
የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነችው ስሟን በሙሉ ለመግለጽ ያልፈለገችው ወይዘሪት ጸዲ፤ ባሳለፍነው ሳምንት አርብ አላማጣ ለመጣው የስኳር በሽታ ታማሚ ወንድሟ ገንዘብ መላኳን ትናገራለች።
“ወንድሜ ወደ አላማጣ የመጣው የስኳር ታማሚ ስለሆነ ምናልባት ካገኘ የኢንሱሊን መድሃኒት መግዣ የሚሆነው ገንዘብ ለመውሰድ ነበር” ያለችው ወ/ሪት ጸዲ፤ ለወንድሟ ከላከችው 10 ሺህ ብር 37 በመቶ እንደተቆረጠባት ትናግራለች።
37 በመቶውም፤ አላማጣ የመጣው ወንድሟ ቅናሽ አገኛለሁ በሚል ሶስት እና አራት ህገ ወጥ የገንዘብ አዘዋዋሪዎችን ለማግኘት ከተንከራተተ በኋላ የተገኘ መሆኑንም ገልጻለች።
ሰዎች ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ወደ አላማጣ መጥተው ለሚደውሉላቸው ዘመዶቻቸው ገንዘብ የሚልኩት፤ የሚቆረጠውን የገንዘብ ልክ ከተስማሙ በኋላ ገንዘቡ ወደሚያደረሱላቸው ሰዎች (ገንዘብ አዘዋዋሪዎች) አካውንት ገንዘብ በማስገባት ነው።
ወ/ሪት ጸዲ፤ ረዥም ጉዞ ተጉዘው ከተለያዩ የትግራይ አከባቢዎች ወደ አላማጣ ለሚመጡ ሰዎች ገንዘብ የሚያደርሱ ህገ-ወጥ የገንዘብ አዘዋዋሪዎች “በትውውቅ እና መለማመጥ ካልሆነ የሚጠይቁት የገንዘብ መጠን ከፍተኛ ነው”፤ “እንደዛም ሆኖ አሁን ብር የለንም እያሉ ሰዎችን የሚያጉላሉ አዘዋዋሪዎች አሉ” ስትልም ትናገራለች።
እንደ ጸዲ ሁሉ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነው አቶ መሓሪ ተስፋይ፤ አላማጣ ለመጡ ቤተሰቦቹ ገንዘብ ሲልክ 40 በመቶ እንደተቆረጠበት ለአል-ዐይን ተናግሯል።
“40 በመቶ እንዲቆረጥ ተስማምተን ብር ለኬያለው ፤ ከላኩት 10 ሺህ ብር 40 በመቶ ተቆርጦ 6 ሺህ ብር ብቻ ቤተሰቦቼ እጅ ላይ ደርሷል” ነው ያለው አቶ መሓሪ።
አቶ መሓሪ ፤ የትራንስፖርት ብር ከየትም ለምኖ ስልክ ለመደወል ወደ አላማጣ የሚመጣው ሰው ከሚላከው ተቆርጦ የሚደርሰው እንዳለ ሁሉ የሚጭበረበር በርካታ ሰው እንዳለም ይናገራል።
“በቅርብ የማውቀው ሰው ከሚልከው 20 ሺህ ብር 40 በመቶ እንዲቆረጥ ከገንዘብ አዘዋዋሪው ግለሰብ ከተስማማ በኋላና ብሩ ወደ አካውንቱ ካስገባለት በኋላ፤ ገንዘብ ይሰጥልኛል ያለው ሰው (አዘዋዋሪው) ስልኩ ዘግቶ ጠፍቷል” ሲልም በአላማጣ የህገ-ወጥ የገንዘብ አዘዋዋሪዎች ችግር ውስጥ ባሉ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ለአብነት አንስቷል።
ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የመገናኘት እድል አለማግኘታቸውን የሚናገሩት ወ/ሪት ጸዲ እና አቶ መሓሪ ተስፋይ “ያለው ሁኔታ እጅግ አስጨናቂ ነው” ሲሉ ይገልጻሉ።
ወ/ሪት ጸዲ፤ “እኔ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ቤተሰቦቼን አግኝቼ አላውቅም፤ ወንድሜ የስኳር ታማሚ ነው፤ቤተሰቦቼ ባጠቃለይ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አላውቅም። “ወንድሜ እንደነገረኝ በመቀሌ ላይ ለከፍተኛ ችግር ተዳርገው በየመንገድ የሚለምኑ ሰዎች በርካታ ናቸው” ብላለች።