“ተጨዋቾቼ የግብ እድሎችን ለማግኝት ከብዷቸው ነበር” - ሩበን አሞሪም
ትላንት ምሽት በተካሄደ ጨዋታ አርሰናል በማንቸስተር ዩናይትድ ላይ በታሪክ 90ኛ ድሉን አሰምዝግቧል

አርሰናል ካላፈው የውድድር አመት ጀምሮ 22 ከማዕዘን የተሻሙ ኳሶችን ወደ ግብ ቀይሯል
በእንግሊዝ ፕርምየር ሊግ በሁለቱ ባላንጣ ቡድኖች መካካል ሲጠበቅ የነበረው ግጥሚያ በአርሰናል 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በኤሜሬትስ ስታድየም 500ኛ ጨዋታቸውን ያደረጉት መድፈኞቹ በማንችስተር ዩናይትድ ላይ በታሪክ 90ኛ ድላቸውን አስመዝግበዋል።
የመድፈኞቹን የማሸነፊያ ግቦች ዊሊያም ሳሊባ እና ጁሪየን ቲምበር አስቆጥረዋል፤ ከቆሙ እና ከማዕዘን ከሚሻሙ ኳሶች ስኬታማ መሆን የቻለው የሰሜን ለንደኑ ክለብ በትላንትናው ጨዋታም ሁለት ከማዕዘን የተነሱ ኳሶችን ወደ ማሸነፍያ ግብነት መቀየር ችሏል።
በዚህም አርሰናል ካላፈው የውድድር አመት መጨረሻ ጀምሮ በአጠቃላይ 22 ከማዕዘን የተሻሙ ኳሶችን በመጠቀም ግብ አስቆጥሯል።
ከአዲሱ አሰልጣኝ እና ታክትኪ ጋር ለመዋሀድ ጥረት እያደረገ የሚገኝው ማንችስተር ዩናይትድ በበኩሉ በውድድር አመቱ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ሽንፈቱን አስተናግዷል።
ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ሩብን አሞሪም ከጨዋታው በኋላ በሰጡት አስተያየት “እነርሱን ለመከላከል የተሻለ መሆን እንዳለብን ቀድመን እናውቅ ነበር በአርሰናል የሜዳ ክፍል ውስጥም ይበልጥ መጫወት እንችል ነበር እርሱን አለማድረጋችን እንድንሸነፍ አድርጓል” ብለዋል።
ማቲስ ዲላይት ያባከነው የግብ እድል የጨዋታውን ቅርጽ ሊቀይረው ይችል እንደነበር የተናገሩት አሰልጣኙ በመጀመርያው አጋማሽ ቡድናቸው ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረጉን ፣ አርሰናል በጣም የተደረጀ ቡድን እንደሆነ እና የግብ እድሎችን ማግኝት ከባድ እንደነበር አንስተዋል።
ከቆሙ ኳሶች የተቆጠሩ ግቦችን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት “አርሰናል የማዕዘን እና ሌሎች የቆሙ ኳሶችን ወደ ግብ መቀየር ላይ የተሻለ አቅም እንዳለው አይተናል፤ በዚህ መነሻ ግብ እንዳይቆጠርበን ለመከላከል ሞክረናል ነገር ግን አርሰናል ለአመታት የቆሙ ኳሶችን ወደ ግብ ሲቀይር የቆየ ክለብ በመሆኑ ለየትኛውም ቡድን ለመከላከል ይከብዳል” ሲሉ ተናግረዋል።
በእንግሊዝ ፕርምየር ሊግ የመጀመርያ ሽንፈታቸውን ያስተናገዱት አሞሪም ቡድናቸው የመሻሻል እና ውጤታማ የመሆን እድል እንዳለው ነው የገለጹት።
ከምሽቱ ጨዋታ 3 ወሳኝ ነጥቦችን ያገኙት መድፈኞቹ ከቼልሲ ጋር እኩል በ28 ነጥብ በመያዝ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ማንችስተር ዩናይትድ በበኩሉ በ19 ነጥብ ከ9ኛ ደረጃ ወደ 11 ተንሸራቷል።