ክለቡ ይህን ያደረገው ተጫዋቾቹን ለማስተማር በሚል ነው ተብሏል
አርሰናል የቡድኑን ተጫዋቾች ንብረት በሌቦች ማሰረቁ ተገለጸ።
የእንግሊዙ አርሰናል እግር ኳስ ክለብ ሆን ብሎ ኪስ አውላቂዎችን በመቅጠር ተጫዋቾቹን አሰርቋል ተብሏል።
የክለቡ አሰልጣኝ ሚካኤል አርቴታ ሀሳብ እንደሆነ የተገለጸው ይህ ውሳኔ አሰልጣኙ እና ተጫዋቾች በነበራቸው እራት ግብዣ ፕሮግራም ላይ ስርቆቱ እንደተፈጸመ ተገልጿል።
ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛ ፋብሪዚዮ ሮማኖቭ እንደዘገበው ከሆነ አሰልጣኝ አርቴታ ተጫዋቾቻቸውን ሆን ብለው ያሰረቁት ለማስተማር በሚል ነው።
አሰልጣኙ በተለይም ተጫዋቾቻቸው ሁሌም ዝግጁ እና ጠንቃቃ መሆን አለባቸው የሚል ትምህርት ማስተማር ፈልገው እንዳደረጉት ተናግረዋል።
ላለፉት ሁለት ዓመታት በማንችስተር ሲቲ ተበልጠው ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁት አርሰናል የተጫዋቾችን ስነ ልቦና ከፍ ማድረግ የሚያስችሉ ስራዎችን በመስራት ላይ ናቸው ተብሏል።
ይሁንና አሰልጣኙ ተጫዋቾቻቸውን ለማስተማር በሚል ካሰረቁ በኋላ ንብረቶቹን ለተጫዋቾች ይመለሱ አይመለሱ በዘገባው ላይ አልተጠቀሰም።
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 2024/25 ውድድር መርሀ ግብር ሊጀመር አንድ ሳምንት ብቻ ቀርቶታል።
የፊታችን እሁድ የእንግሊዝ ኮሙኒቲ ሽልድ ዋንጫ በሁለቱ የማንችስተር ከተማ ክለቦች መካከል ይካሄዳል።
በሳምንቱ ደግሞ ነሀሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር መክፈቻ ጨዋታ በማንችስተር ዩናይትድ እና ፉልሀም መካከል ይካሄዳል።