ሁለቱ የእንግሊዝ ተቀናቃኝ ቡድኖች አርሰናል እና ማንችስተር ለ242ኛ ጊዜ ይገናኛሉ
በአሞሪም አሰልጣኝነት የውጤት መሻሻል ያሳየው ማንቸስተር ዩናይትድ ምሽት በኤሜሬትስ አርሰናልን ይገጥማል
ሁለቱ ቡድኖች በተገናኙባቸው አጠቃላይ ጨዋታዎች ቀያይ ሰይጣኖቹ 99 ጊዜ ሲያሸንፉ መድፈኞቹ 89 ጨዋታዎችን በድል አጠናቀዋል
የአንድ ከተማ ቡድኖች ባይሆኑም ተቀናቃኝነታቸው ከደርቢ ጨዋታዎች በላይ ከፍተኛ ፉክክር የሚደረግበት ነው፡፡
አርሰናል እና ማንችስተር ዩናይትድ በእንግሊዝ ፕርምየር ሊግ ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙት በጥቅምት በ1894 ሲሆን፤ በዚህ ጨዋታ ሶስት አቻ ተለያይተዋል። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እስካለፈው ግንቦት ወር ድረስ 241 ጨዋታዎችን አድርገዋል፡፡
በነዚህ ጨዋታዎች መድፈኞቹ 89 ጊዜ ሲያሸንፉ ቀያይ ሰይጣኖቹ በ10 ጨዋታ ልቀው 99 ጨዋታዎችን በድል ተወጥተዋል፤ 53 ግጥሚያዎች ደግሞ በአቻ የተለያዩባቸው ናቸው፡፡
በሚኬል አርቴታ አሰልጣኝነት ያለፉትን የውድድር ዘመናት በደረጃ ሰንጠረዡ እንዲሁም በሊጉ ተፎካካሪ የሆነው አርሰናል የሊጉን ዋንጫ ካነሳ ሁለት አስርተ አመታት ተቆጥረዋል፡፡
በሰር አሌክስ ቨርጉሰን ዘመን በሊጉ እና በሌሎች አለምአቀፋዊ ውድድሮች ነግሶ የቆየው ማንችስተር ዩናይትድ በበኩሉ ከአሰልጣኙ ስንበት በኋላ የተለያዩ አስልጣኞችን ቢለዋወጥም ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ አደጋች ሆኖበታል፡፡
በአሁናዊ አቋሙ ፖርቹጋላዊውን አሰልጣኝ ሩብን አሞሪምን በመሾም የተለየ የቡድን መዋቅር እና አሰላለፍ በመከተል ወደ ሊጉ ተፎካካሪነት መድረክ ለመመለስ ጥረት ላይ ይገኛል፡፡
ዩናይትድ በሊጉ በ9 ነጥቦች ዝቅ ብሎ ከሚገኘው አርሰናል ጋር በኤሜሬትስ ስታድየም ወሳኝ እና ተጠባቂ ጨዋታውን ያከናውናል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ሁለቱም ቡድኖች ተጋጣሚዎቻቸውን 5ለ2 እና 4ለ0 በሆነ ውጤት መርታት ችለዋል፡፡
መድፈኞቹ ለመጨረሻ ጊዜ በሁሉም የውድድር መድረኮች ያደረጓቸውን ሶስት ጨዋታዎች በሶስት እና ከዛ በላይ የሆነ ጎል በማስቆጠር አሸንፈዋል፡፡
ከብሬንትፎርድ እና ብራይተን ቀጥሎ በሜዳው ያለመሸነፍ ሪከርድን ይዞ የቀጠለው ቡድኑ በኤምሬትስ ካደረጋቸው ያለፉት 7 ጨዋታዎች ስድስቱን ያሸነፈ ሲሆን በሜዳው ግብ በማስቆጠርም ከፍተኛ ምጣኔ ያለው ቡድን ነው፡፡
ኤቨርተንን በጆሺዋ ዘርክዚ እና በማርከስ ራሽፎርድ ሁለት ሁለት ግቦች አሸነፎ ደረጃውን ወደ 9 ከፍ ያደረገው ዩናይትድ ከነገው ተቀናቃኙ አርሰናል ያለው የውጤት ልዩነት ስድስት ብቻ ነው፡፡
ካለፉት 4 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች 8 ነጥቦችን መሰብሰብ የቻሉት ቀያይ ሰይጣኖቹ በሩብን አሞሪም አሰልጣኝነት ከአዲስ ታክትኪ እና አሰላለፍ ጋር ለመዋሀድ ጥረት እያደረጉ ከኤሪክ ቴን ሀግ ዘመን የተሻለ መነቃቃትን እያሳዩ ቀጥለዋል፡፡
ለመጨረሻ ጊዜ ከአርሰናል ጋር ያደረጓቸውን ሶስት ጨዋታዎች መሸነፋቸው እንዲሁም ከ2019 3ለ1 የኤፍኤካፕ ዋንጫ አሸናፊነት ወዲህ በኤሜሬትስ አለማሸነፋቸው የነገውን ጨዋታ ለዩናይትድ ከባድ እንደሚያደርገው የእንግሊዝ ጋዜጦች ጽፈዋል፡፡
አርሰናል የነገውን ጨዋታ የሚያሸንፉ ከሆነም በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በተከታታይ አራት ጨዋታዎች በዩናይትድ ላይ ድል መቀዳጀቱን ያውጃል፡፡
ጉዳት እና አሰላለፍን በተመለከተ መድፈኞቹ ጋብሪኤል ማጋሌሽን ከስፖርቲንግ ጋር በነበረው ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ በጉዳት አጥተውታል፡፡ በዚህ ሰአት ብራዚላዊው ተጫዋች ለነገው ጨዋታ መድረሱ በጥያቄ ላይ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም ሚኬል ሜሪኖ የጉልበት፣ ቶማስ ፓርቴይ የጡንቻ እና ማይልስ ሌዊስስኬሊ ባልተገለጸ ጉዳት ላይ ይገኛሉ፡፡
በዩናይትድ በኩል አምበሉ ብሩኖ ፈርናንዴዝ ለነገው ጨዋታ መድረስ ላይ ትልቅ ስጋት ገጥሟቸዋል፡፡
ብሩኖ በኤቨርተኑ ጨዋታ በ65ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ከወጣ በኋላ ቁርጭምጭሚቱ በበረዶ ተሸፍኖ ታይቷል፤ሆኖም አሞሪም ለዚህ ጨዋታ ብቁ ይሆናል ብሎ እንደሚጠብቅ አረጋግጧል፡፡
ነገርግን በእርግጠኝነት የማይገኙ ሁለት ተጫዋቾች ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ እና ኮቢ ማይኖ ሲሆኑ ሁለቱም ከኤቨርተን ጋር በነበረው ግጥሚያ ከነገው ጨዋታ በቅጣት የሚያርቃቸውን ቢጫ ካርዶችን ተመልክተዋል፡፡
ሃሪ ማጉየር ከጉዳት በኋላ በተከላካይነት የማርቲኔዝን ስፍራ ይይዛል። ሌኒ ዮሮ ለኤሜሬትሱ ጨዋታ ሊሰለፍ እንደሚችል ይጠበቃል። ጆኒ ኢቫንስ እና ቪክቶር ሊንደሎፍ በጉዳት በነገው ጨዋታ የማይኖሩ ናቸው፡፡