ሚኬል አርቴታ በአርሰናል ቤት ለተጨማሪ 3 ዓመታት ለመቆየት ውላቸውን አራዘሙ
አሰልጣኙ ከ20 ዓመት በኋላ ቡድኑን ወደ ሊጉ ዋንጫ ክብር ለመመለስ ጥረት እያደረጉ ነው
አዲሱ የውድድር ዘመን ሲጠናቀቅ ፒኤስጂና ባርሴሎና አርቴታን ለመውሰድ ፍላጎት ነበራቸው
ስፔናዊው አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ በአርሰናል እስከ 2027 የሚያቆያቸውን አዲስ ውል ፈረሙ፡፡
በ2019 የቀድሞውን የክለቡን አሰልጣኝ ኡና ኤምሬ በመተካት ቡድኑን ማሰለጠን የጀመሩት አርቴታ በ2019/20 ኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን መድፈኞቹ እንዲያነሱ ማድረግ ችለዋል፡፡
የማንችስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ምክትል ሆነው ሲሰሩ የነበሩት አሰልጣኙ ወደ አርሰናል ከመጡ በኋላ ቡድኑ የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ እና ተፎካካሪ እንዲሆን ማስቻላቸው ይነገርላቸዋል፡፡
አርቴታ ከ2003/2004 የውድድር ዘመን በኋላ አርሰናልን ወደ ሊጉ ዋንጫ ባለቤትነት ለመመለስ እያደረጉ በሚገኙት ጥረት ያለፉትን ሁለት የውድድር ዘመኖች በሁለተኛነት ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡
በዘንድሮው የውድድር አመት ከክለቡ ጋር ያለው ኮንትራት የሚጠናቀቅ መሆኑን ተከትሎ ፒኤስጂ እና ባርሴሎና አርቴታን ለመውሰድ ፍላጎት ያሳዩ ክለቦች እንደነበሩ ተሰምቷል፡፡
ቡድኑ የአሰልጣኙን ኮንትራት ያራዘመበት ውሳኔ አርሰናል ከ20 አመታት በኋላ የፕርምየር ሊግ ዋንጫ እንዲያነሳ አርቴታ ትክክለኛው ሰው መሆኑን እንደሚያምን የሚያመላክት ነው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የስፖርት ተንታኞች በበኩላቸው ባለፉት 6 አመታት ስፔናዊው አሰልጣኝ አርሰናል ላይ እያሳየ የሚገኝው ለውጥ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው ክለቡ ተጨማሪ ጊዜን ለመስጠት መወሰኑም ትክክለኛ ነው ብለዋል፡፡
መድፈኞቹ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ባደረጓቸው ሶስት ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፈው አንዱን አቻ በመውጣት በሊጉ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡
የቀድሞዎ የቡድኑ አማካይ ተጫዋች የነበረው አርቴታ በአርሰናል ቤት 150 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ መጫወት ችሏል፡፡
ራሂም ስተርሊንግ ፣ ማይክል ሜሪኖ እና ሪካርዶ ካላፊዮሪን ወደ ስብስባቸው ማቀላቀል የቻሉት መድፈኞቹ ምንም እንኳን አጥቂ ማስፈረም ነበረበቸው የሚለው ላይ ጥያቄ ቢኖርም በውድድር ዘመኑ ብርቱ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁት የእንግሊዝ ክለቦች ተርታ ይገኛሉ፡፡