በኬንያ የአርሰናል ደጋፊዎች ክለባቸው ማሸነፉን ተከትሎ ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ
ደጋፊዎቹ በናይሮቢ ባለ አንድ ቤተ ክርስቲያን የምስጋና መዝሙር በጋራ ዘምረዋል
አርሰናል ባሳለፍነው ቅዳሜ ክሪስታል ፓላስን 5 ለ0 ማሸነፉ ይታወሳል
በኬንያ የአርሰናል ደጋፊዎች ክለባቸው ማሸነፉን ተከትሎ ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ፡፡
የእንግሊዙ አርሰናል ባሳለፍነው ቅዳሜ በሜዳው ከክርስቲያል ፓላስ ጋር ያደረገውን ጨዋታ 5 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
በኬንያ መዲና ናይሮቢ ያሉ የአርሰናል ደጋፊዎች የክለባቸውን ማሸነፍ አስመልክተው ፈጣሪያቸውን በጋራ አመስግነዋል፡፡
ካፒታል ኤፍኤም እንደዘገበው ከሆነ ደጋፊዎቹ ክለባቸው በማሸነፉ በናይሮቢ ከተማ ውስጥ ባለ አንድ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው አመስግነዋል፡፡
የአርሰናል ክለብን ማልያ በመልበስ ወደ ቤተ ክርስቲያን የመጡት እነዚህ ደጋፊዎች በጋራ ሲዘምሩ የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ብዙ ተመልካች አግኝቷል፡፡
የኬንያዊያን አርሰናል ደጋፊዎች ድርጊት ዋነኛ የማህበራዊ አጀንዳ የሆነ ሲሆን አንዳንዶች የደጋዎቹ ድርጊት የተጋነነ እና ያልተገባ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡
ደጋፊዎቹ ክለባቸው አርሰናል በፍጹም የበላይነት ክሪስታል ፓላስን ማሸነፉ እና ከአምናው አሸናፊ ማንችስተር ሲቲ ጋር እኩል መሆናቸው እንዳስደሰታቸው እና በቀጣይም በዚህ ብቃቱ እንደሚቀጥል ተስፋ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡
የኡጋንዳ ፖሊስ 20 የአርሰናል እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎችን አሰረ
አርሰናል በአፍሪካ ተወዳጁ የአውሮፓ ክለብ ሲሆን ከደጋፊዎች ጋር በተያያዘ ለየት ያሉ ክስተቶችን በማስተናገድ ይታወቃል፡፡
ከዚህ በፊት በኡጋንዳ ያሉ የአርሰናል ደጋፊዎች ክለባቸው ማሸነፉን ተከትሎ ደስታቸውን አጋነዋል በሚል የሀገሪቱ ፖሊስ የተወሰኑ የክለቡ ደጋፊዎችን ማሰሩ አግራሞትን ፈጥሮ ነበር፡፡
የአፍሪካ መሪዎች ሳይቀር አርሰናልን በመደገፍ የሚታወቁ ሲሆን የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ አሰልጣኞች እንዲባረሩ አስተያየት ሲሰጡ ይታወሳሉ፡፡
የሰሜን ለንደኑ አርሰናል ከፕሪሚየር ሊጉ መሪ ሊቨርፑል አምስት ነጥቦች ርቆ በፔፕ ጋርዲዮላው ሲቲ ጎል ተበልጦ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ አስተን ቪላ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡