“አርቴታ የአርሰናልን አስተሳሰብ በመቀየር አስደናቂ ስራ ሰርቷል”- ፋብሪጋስ
አርሰናል ለአርቴታ የሰጠው ጊዜ ሌሎች ክለቦች ሊማሩበት የሚገባ መሆኑም ጠቁሟል ፋብሪጋስ
ፋብሪጋስ፤ አርቴታ በማንቸስተር ሲቲ ቤት ከጋርዲዮላ ጋር መስራቱ እንደጠቀመው ተናግሯል
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በትናትናው ዕለት በተካሄደው ጨዋታ የአርሰናል፤ ማንችስተር ዩናይትድን 3ለ2 ማሸነፉን ተከትሎ በ50 ነጥብ መሪነቱን አጠናክሯል።
አርሰናል በውድድር ዘመኑ እያሳየ ካለው ብቃት በስተጀርባ የስፔናዊው አሰልጣኝ ማይክል አርቴታ ሚና ትልቅ እንደሆነም በርካቶች ያነሳሉ።
ለክለቡ መለወጥ የአርቴታ ድርሻ ከፍተኛ ነው የሚለውን ኃሳብ ከሚጋሩ የስፖርት አዋቂዎች አንዱ የቀድሞ የአርሰናል ተጫዋች ሴስክ ፋብሪጋስ ነው።
የቀድሞ የአርሰናል አማካኝና አምበል ሴስክ ፋብሬጋስ አርቴታ የአርሰናልን አስተሳሰብ ቀይሮታል ሲል ለአሰልጣኙ ያለውን አድናቆት ገለጿል።
ሴስክ ፋብሪጋስ ከስካይ ስፖርት ጋር በነበረው ቆይታ እንደተናገረው “አርቴታ ተጨዋቾችን የሚያነሳሰበት እና የሚረዳበት መንገድ አይተናል፤ በዚህ አስደናቂ ስራ ሰርቷል” ብሏል።
ማይክል አርቴታ የአርሰናል አሰልጣኝ ሆኖ ሲቀጠር በማንቸስተር ሲቲ ረዳት ሆኖ ከመስራት በዘለለ ምንም ልምድ እንዳልነበረው ያስታወሰው ፋብሪጋስ፤ “በማንቸስተር ሲቲ ቤት ከጋርዲዮላ ጋር መስራቱ እንደጠቀመው ግልጽ ነው” ሲልም ተናግሯል።
"በቅርብ ጊዜ በስልጠናው ቦታ ተገኝቼ ነበር እና ሁሉም ነገር በጣም ተለውጧል፤ በፊት እዚያ እንዳልነበርኩ ሆኖ ነው ተሰማኝ። የስልጠና ቦታው ስራ አስኪያጅ እንደነገረኝ ከሆነ 95 በመቶ የሚሆኑት ለውጦች የአርቴታ ናቸው” ሲልም አክሏል።
"አርቴታ ቬንገር ከለቀቁ በኋላ የክለቡን አመለካከት ለውጦታል፤ በስልጠናው ቦታ ላይ ብዙ አዎንታዊ መልዕክቶችን፣ ብዙ ትላልቅ መገልገያዎችን፣ የተሻሉ መሳሪያዎች፣ ሜዳዎች የተሻሉ ናቸውም ነው” ያለው የቀድሞ የክለቡ አማካኝና አምበል ሴስክ ፋብሪጋስ።
መድፈኞቹ ለሁለት ተከታታይ የውድድር ዘመናት ስምንተኛ ሆነው ማጠናቀቃቸውን ያስታወሰው ፋብሪካጋስ፤ ክለቡ አሁን እያሳየው ያለው ብቃት አበረታች መሆኑም ገልጿል።
ካለ ምንም ወጪ የተገኙ እንደ ሳካ እና ንከቲያህ ያሉ ከአካዳሚው ተጫዋቾች እያሳዩት ያለው ድንቅ ብቃት አርሰናልን እጅጉን ውጤታማ እንዲሆን እንዳደረገውም ጭምር በመግለጽ።